Monday, August 22, 2011

ቡና ያለ ሀገሩ



ኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝቡን ማኅበራዊ ሕይወት ካቆሙት ነገሮች አንዱ የቡናው ሥርዓት ነው፡፡ ምንም እንኳን
ቡና ጥሩ ነበር ለማግኛ ወዳጅ
ቁርሱ የሰው ሥጋ መሆኑ ነው እንጂ
የሚሉ የግድግዳ ጥቅሶች የሚነቅፉት ነገር ቢኖራቸውም ቡና ባይኖር ኖሮ ግን እናቶቻችን የመወያያ፣ የመጠያየቂያ እና ጭንቀትን የመካፈያ መንገድ አይኖራቸውም ነበር፡፡
 በዚህም የተነሣ በባሕሉ ቡና አፍልቶ የሚጠራ ይመሰገናል፣ ይወደዳል፣ ይመረቃል፡፡ አንዳንዴም መንደሩ በሙሉ በተራ ቡና ያፈላል፡፡ ቡና ድኻ እና ሀብታም አይልምና፡፡
እንዲያውም «ሴቶች ቡና ላይ ወንዶች ጠጅ ቤት ተገናኝተው የወሰኑትን ማንም አይፈታውም» ይባላል፡፡ በቀበሌ ስብሰባ፣ በቴሌቭዥን ንግግር፣ በኮንፈረንስ እና በዐውደ ጥናት የተለፈፈውን ሴቶቹ ቡና ላይ ወን ዶቹም ጠጅ ቤት ሰብሰብ ብለው «ተወው እባክህ፣ተይው እባክሽ» ከተባባሉበት ቆለፉት ማለት ነው፡፡
አንድ ወዳጄ እንዲያውም ኤይድስን ለመዋጋት ለሻማ፣ ለቲሸርት እና ለቆብ ይህንን ሁሉ ገንዘብ ከማ ዋጣት ለእናቶቻችን የቡና መጠጫ ጥቂት ቢሰጧቸው ኖሮ ከዐውደ ጥናቱ በላይ ውጤት ያለው ውይይት ይደረግ ነበር ብሎኛል፡፡
እዚህ እኔ ያለሁበት ዚምባብዌ ግን ቡና ያለ ሀገሩ መጣና ጉድ ፈላበት፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ ኢትዮጵ ያዊት እናት በባልዋ ሥራ ምክንያት ሐራሬ ትመጣለች፡፡ የሐራሬ ቤቶችን ብታዩዋቸው ያስቀኗችኋል፡፡ የአንዱ ሰው ግቢ በትንሹ አምስት ካሬ ሜትር ቦታ ነው፡፡ አቤት ይሄ ግቢ እኛ ሀገር ቢገኝ ስንት ኮንዶሚኒየም ይሠራበት ነበር? አልኩና ቀናሁ፡፡ (ኦፍ ዘሪከርድ እንነጋገርና አዲስ አበባ ውስጥ ባዶ ቦታ ያለው ብቻ ሳይሆን ፀጉር አልባ የሆነ ባዶ ራስ (ራሰ በራ) ሰውም ይሠጋል አሉ፡፡ ጭንቅላቱን በሊዝ እንዳይመሩበት፡፡ እዚህ ብዙ ራሰ በራ ሐበሾች አየሁ፡፡ ፈርተው መጡ እንዴ)
ኢትዮጵያዊቷ የቤት እመቤት እዚህ ሰፊ ግቢ ውስጥ ብቻዋን ውሎ ማደር ሲሰለቻት ጊዜ እንደ ባህልዋ ቡና ማፍላት ፈለገች፡፡ ችግሩ ማን ያጣጣታል? የሚለው ነው፡፡
እዚያ ቤት የተቀጠረች አንዲት ዚምባቤያዊት ሠራተኛ አለቻት፡፡ እዚህ ሀገር የቤት ሠራተኞች ከሰኞ እስከ ዓርብ እስከ 11 ሰዓት፣ ቅዳሜ እስከ ሰባት ሰዓት ነው የሚሠሩት እሑድ አና ቅዳሜ ከሰዓት ዕረፍት ናቸው፡፡ መኖርያቸውም ለብቻ ግቢው ውስጥ የተሠራ ቤት ነው፡፡
ያቺ ኢትዮያዊት የቤት እመቤት ሠራተኛዋ ሥራ ስትጨርስ ትጠራትና ወደ አመሻሽ ቡና ይጠጣሉ፡፡ ቅዳሜ ከሰዓትም ባለቤቷ ሳይኖር ትጠራትና አብረው ወሬ እየሰለቁ ቡና ይጠጣሉ፡፡
በወሩ መጨረሻ ለቤት ሠራተኛዋ ደመወዝዋን ለመክፈል ትጠራትና የተነጋገሩትን ደመወዝ ትከፍላታለች፡፡ ይኼኔ ሠራተኛዋ
«የሚቀር ገንዘብ አለኝ» አለች፡፡
«ምን ጠየቀች የቤት እመቤቷ፡፡
«ኦቨር ታይም የሠራሁበት»
«መቼ ምን ሠራሽ»
«በዚህ በዚህ በዚህ ቀን ካንቺ ጋር ቁጭ ብዬ ቡና የጠጣሁበት»
«እንዴ እኔ ብቻ ነኝ እንዴ የጠጣሁት አንቺም ጠጥተሻልኮ»
«ቢሆንም ላንቺ ብዬ እንጂ እኔ ፈልጌ አልጠጣሁም፤ አንቺን ለማዝናናት ነው የተቀመጥኩት እንጂ እኔ ቡና ለመጠጣት መች ከሁለት ደቂቃ በላይ ይፈጅብኛል»
«ወይ አዲስ አበባ ወይ ሀገሬ ሆይ
 ቡና አጣጭ እንደ እናት ይናፍቃል ወይ»
 ሳትል አትቀርም የቤት እመቤቷ፤ ቡና አፍይ ከሚመሰገንበት ሀገር ቡና ለማጣጣት ኦቨር ታይም ወደሚከፈልበት ሀር ስትገባ፡፡ ምንም ማድረግ አልቻለችም፡፡ ሂሳቡን ከፈላ ቡና መጠጣቱን ተወቺው፡፡ ቡና ያለ ሀገሩ ገብቶ እንዲህ መከራውን አየላችሁ፡፡

No comments:

Post a Comment