Tuesday, November 15, 2011

እመቤታችን ከማረፏ ከሰዓታት በፊትና በኋላ ምን ሆነ?

----------
ማርያም ስጋኪ ዘተመሰለ ባሕርየ
ተሓፍረ ሞት አኮኑ ሶበ ነጸረ ወርእየ
እንዘ በደመና ብሩህ የዐርግ ሰማየ
እንኳን አደረሰን

እመቤታችን በእናት አባቷ ቤት ሦስት ዓመት፣ አሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ /ዘጠኝ ወር በቤተ ዮሴፍ/፣ ከመድኃኒታችን ጋር ሰላሣ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ፣ በቤተ ዮሐንስ አሥራ አምስት ዓመት፤ ጠቅላላ ስድሳ አራት ዓመት በዚህ ምድር ኑራለች::

ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ለአገልግሎት ወደ ኤፌሶን በሄደበት ወቅት የቤተ መቅደስ አለቆች ልጆች የነበሩ ደናግል እግሯን እያጠቡ እየተላላኩ ያገለግሏት ነበር:: እመቤታችን ጐልጐታ በሚገኝው የመቃብር ቦታ እየሄደችም አዘውትራ ትጸልይ ነበር:: መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም በመቃብሩ በምትጸልይበት ጊዜ ከዚህ ዓለም በሥጋ ስለምታርፍበት ሁኔታ ከነገራት በኋላ ታመመች:: ያን ጊዜ አገልጋዮቿና ጎረቤቶቿ ሁሉ በአንድነት ተሰበሰቡ ብዙ ድውያንም ወደእርስዋ እየመጡ ያመሰግኗትና ይፈወሱም ነበር:: እመቤታችንም ደስ ብሏት ትባርካቸዋለች::

Monday, August 22, 2011

ጾመ ፍልሰታ።


ነሐሴ ፩ ቀን ፳፻ ዓ∙ ም∙


እንኳን ለጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሰዎ። ጾመ ፍልሰታ እንደሚታወቀው በአገራችን ዐዋቂዎች ብቻ ሳይሆኑ ሕፃናት ሳይቀሩ የሚጾሙት ጾም ነው። ጾሙም ብዙ ጸጋና በረከት የሚያሰጥ ነው።
ይህ ጾም እንዴት እንደ ተጀመረ ታሪኩን የሚገልጸውን የድምፅ ፋይል ከድምፅ ማኅደር ማውረድ ይችላሉ። የድምፅ ፋይሉ የተቀረጸው በ፲፱፻፺፰ ዓ፤ ም፤ ሲሆን ያስተማሩትም አለቃ አያሌው ታምሩ ናቸው።
አባታችን ለጾመ ፍልሰታ ልዩ ፍቅር የነበራቸው ሲሆን በዚህ ጾም ጊዜ ከአባቶቻቸው እንደ ወረሱት በየዕለቱ ማለዳ ውዳሴ ማርያምንና ቅዳሴ ማርያምን በአንድምታ የመተርጐም ልምድ ነበራቸው። በየዕለቱ ማታ ማታም እንደ ዘወትር ሁሉ ውዳሴ ማርያምን በዜማ ያደርሱ ነበር። በዜማ ያደርሱት ከነበረው በ፲፱፻፺፬ ዓ፤ ም፤ የተቀረፀውን ከድምፅ ማኅደር ውስጥ ማውረድ ይችላሉ። እንዲሁም በ፲፱፻፺፰ ዓ፤ ም፤ ጾመ ፍልሰታ የተቀረጸውን የውዳሴ ማርያም የአንድምታ ትርጕም ከዚሁ ከድምፅ ማኅደር ውስጥ ማውረድ ይችላሉ።
አምላካችን ጾሙን የተባረከ ያድርግልን።

የሮማ ካበመቃወም የቀረበ መግለጫ።ቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለፓፓ ፒየስ ፲፪ኛ የቅድስና መዓርግ ለመስጠት ማሰቧን


የተወደዳችሁ ምእመናን! የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንዳስቀመጠው የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሃይማኖት ከኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያን ከተለየችበት ጊዜ አንሥቶ የሮማን የቄሣር መንግሥት ጉልበት በማድረግ ካቶሊካውያን ያልሆኑ ክርስቲያኖችን በተለያዩ አሠቃቂ መንገዶች ከማጥቃት የቦዘነችበት ጊዜ የለም። ይልቁንም የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን። ይህም ግብሯ በዐፄ ሱስንዮስ ጊዜ በነበረው የሃይማኖት ጦርነት፥ ኋላም በዐድዋ ጦርነትና በ፭ቱ ዓመት የፋሺስት ጦርነት ጊዜ የታየና በታሪክ የተመዘገበ ነው። እነዚህ ጦርነቶች ሁሉ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን አወንታና ቡራኬ ያገኙ ነበሩ። ይልቁንም በ፲፱፻፳፰ ዓ. ም. የኢጣሊያ ጦር በፋሺስቱ መሪ በቤኒቶ ሙሶሊኒ አዛዥነት ኢትዮጵያን ለመውረር በተንቀሳቀሰ ጊዜ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲንያና በጊዜው የነበሩት ፓፓዋ ፒየስ ፲፪ኛ ጦርነቱ የተቀደሰ መሆኑን በመጥቀስ ሠራዊቱን መባረካቸውና የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳትና ካህናትም የተለያየ ልገሣ ለፋሺስት ጦር ማድረጋቸውን ታሪክ መዝግቦታል።
የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያን እጅ ለማድረግ ባደረገችው የረጅም ጊዜ ትግል ይልቁንም ከ፲፱፻፳፰ ዓ. ም. - ፲፱፻፴፫ ዓ. ም. ከሙሶሊኒ ጋር ተባብራ በጥቁር ሸሚዝ ለባሽ ፋሺስት ጦረኛዋ የፈጸመችው ግፍ፥ በተከለከለ የመርዝ ጋዝና የአውሮፕላን ድብደባ የኢትዮጵያን ሕዝብ በመጨረስ ያሳየችው ጎምዛዛና መራር አድራጎት እንኳን ለኢትዮጵያውያን ለባዕዳን ሕሊና የሚሰቀጥጥ እንደ ነበር ታሪክ መዝግቦታል።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የታሪክ ጸሓፊዎችና ተመራማሪዎች ብዙ የጻፉ ሲሆን አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩም በተለያዩ መጻሕፍቶቻቸውና በተለያዩ አጋጣሚዎች ባስተላለፏቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች አማካይነት ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ገለጻ አቅርበዋል። ለምሳሌ ያህል መስከረም ፲፩ ቀን ፲፱፻፹፱ ዓ. ም. በወጣው ማዕበል አማካይነት፤ «ታሪክ ይናገራል፤ መልስም ይጠብቃል፤» በሚል ርእስ ያቀረቡትን ጽሑፍ ከዚህ ማየት ይቻላል።
ይህ በንዲህ እንዳለ በቅርቡ የአሁኑ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፓፓ ቤኔዲክት ፲፮ኛ፤ በ፪ኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ለነበሩት ፓፓ ፒየስ ፲፪ኛ የቅድስና መዓርግ ሊሰጧቸው መሆኑ ተሰምቷል። (Pope John Paul II and Pius XII move closer to sainthood – BBC News, Vatican defends move to beatify wartime pope – MSNBC)
ከላይ እንደ ተጠቀሰው ፓፓ ፒየስ ፲፪ኛ በ፲፱፻፳፰ ዓ. ም. የፋሺስት ጦር ኢትዮጵያን ለመውረር በተንቀሳቀሰበት ጊዜ ጦርነቱ የተቀደሰ ነው በማለት በሰጡት ቡራኬ መሠረት፤ በ፭ቱ ዓመት ተጋድሎ የኢጣሊያ ጦር ባደረገው ጭፍጨፋ የካቲት ፲፪ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ. ም. በአዲስ አበባ ከተማ በተደረገው ጭፍጨፋ ብቻ ከሦስት መቶ ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ማለቅ፤ በተጨማሪም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በሕዝብ ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ፥ በተለያዩ የኢትዮጵያ ገዳማት በደብረ ሊባኖስ፥ በዲማ፥ በዋልድባ፥ እንዲሁም በተለያዩ የኢትዮጵያ ገዳማት በሚገኙ መነኮሳት ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ፥ የታላላቆቹ አባቶች የአቡነ ጴጥሮስና የአቡነ ሚካኤል መሥዋዕትነት፥ እነ ራስ ደስታ ዳምጠውን የመሳሰሉ የነጻነት ዐርበኞች መሥዋዕትነት ፤ የአብያተ ክርስቲያን መቃጠል፥ የንዋየ ቅድሳት ምዝበራና ዘረፋ በታሪክ መዛግብት ተመዝግቦ የፋሺትን ጨካኝነት፥ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንንና የፓፓዋን ለተቀደሰው የሰው ልጆች ሕይወት ያላቸውን ደንታ ቢስነት እየመሰከረ እያለ እንደገና አሁን፤ ግፈኛውን የፋሺስት ጦር፤ «የምታካሂደው የተቀደሰ ጦርነት ነውና ግፋ ቀጥል፤» በማለት ቡራኬ የሰጡትን ፓፓ ፒየስ ፲፪ኛ «ቅዱስ» ብሎ መጥራት የሰውን ልጅ ክብር ማዋረድ ከመሆኑም በላይ የክርስትናን ሃይማኖት የሚጻረር በመሆኑ፤ ይህን ዐሳብ የኢትዮጵያንና የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ክብርና ነጻነት ለመጠበቅ በተደረጉ ተጋድሎዎች አጥንታቸውን በከሰከሱ፥ ደማቸውን ባፈሰሱ ኢትዮጵያውያን ስምና በኢትዮጵያ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በጥብቅ የምንቃወም መሆኑን እንገልጻለን። ስለሆነም ፓፓ ቤኔዲክት ፲፮ኛ ለፓፓ ፒየስ ፲፪ኛ የቅድስና መዓርግ ለመስጠት ያሰቡትን ዐሳብ እንዲሰርዙ እንጠይቃለን። እንዲሁም ይህንን የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ዐሳብ በመቃወም በተለያዩ አቅጣጫዎች በመሰለፍ ድምፃቸውን በማሰማት ላይ ላሉ ወገኞች ያለንን አጋርነት እንገልጻለን።
አምላካችን አገራችንን ኢትዮጵያን ይጠብቅልን፤ አሜን።

ቡና ያለ ሀገሩ



ኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝቡን ማኅበራዊ ሕይወት ካቆሙት ነገሮች አንዱ የቡናው ሥርዓት ነው፡፡ ምንም እንኳን
ቡና ጥሩ ነበር ለማግኛ ወዳጅ
ቁርሱ የሰው ሥጋ መሆኑ ነው እንጂ
የሚሉ የግድግዳ ጥቅሶች የሚነቅፉት ነገር ቢኖራቸውም ቡና ባይኖር ኖሮ ግን እናቶቻችን የመወያያ፣ የመጠያየቂያ እና ጭንቀትን የመካፈያ መንገድ አይኖራቸውም ነበር፡፡
 በዚህም የተነሣ በባሕሉ ቡና አፍልቶ የሚጠራ ይመሰገናል፣ ይወደዳል፣ ይመረቃል፡፡ አንዳንዴም መንደሩ በሙሉ በተራ ቡና ያፈላል፡፡ ቡና ድኻ እና ሀብታም አይልምና፡፡
እንዲያውም «ሴቶች ቡና ላይ ወንዶች ጠጅ ቤት ተገናኝተው የወሰኑትን ማንም አይፈታውም» ይባላል፡፡ በቀበሌ ስብሰባ፣ በቴሌቭዥን ንግግር፣ በኮንፈረንስ እና በዐውደ ጥናት የተለፈፈውን ሴቶቹ ቡና ላይ ወን ዶቹም ጠጅ ቤት ሰብሰብ ብለው «ተወው እባክህ፣ተይው እባክሽ» ከተባባሉበት ቆለፉት ማለት ነው፡፡
አንድ ወዳጄ እንዲያውም ኤይድስን ለመዋጋት ለሻማ፣ ለቲሸርት እና ለቆብ ይህንን ሁሉ ገንዘብ ከማ ዋጣት ለእናቶቻችን የቡና መጠጫ ጥቂት ቢሰጧቸው ኖሮ ከዐውደ ጥናቱ በላይ ውጤት ያለው ውይይት ይደረግ ነበር ብሎኛል፡፡
እዚህ እኔ ያለሁበት ዚምባብዌ ግን ቡና ያለ ሀገሩ መጣና ጉድ ፈላበት፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ ኢትዮጵ ያዊት እናት በባልዋ ሥራ ምክንያት ሐራሬ ትመጣለች፡፡ የሐራሬ ቤቶችን ብታዩዋቸው ያስቀኗችኋል፡፡ የአንዱ ሰው ግቢ በትንሹ አምስት ካሬ ሜትር ቦታ ነው፡፡ አቤት ይሄ ግቢ እኛ ሀገር ቢገኝ ስንት ኮንዶሚኒየም ይሠራበት ነበር? አልኩና ቀናሁ፡፡ (ኦፍ ዘሪከርድ እንነጋገርና አዲስ አበባ ውስጥ ባዶ ቦታ ያለው ብቻ ሳይሆን ፀጉር አልባ የሆነ ባዶ ራስ (ራሰ በራ) ሰውም ይሠጋል አሉ፡፡ ጭንቅላቱን በሊዝ እንዳይመሩበት፡፡ እዚህ ብዙ ራሰ በራ ሐበሾች አየሁ፡፡ ፈርተው መጡ እንዴ)
ኢትዮጵያዊቷ የቤት እመቤት እዚህ ሰፊ ግቢ ውስጥ ብቻዋን ውሎ ማደር ሲሰለቻት ጊዜ እንደ ባህልዋ ቡና ማፍላት ፈለገች፡፡ ችግሩ ማን ያጣጣታል? የሚለው ነው፡፡
እዚያ ቤት የተቀጠረች አንዲት ዚምባቤያዊት ሠራተኛ አለቻት፡፡ እዚህ ሀገር የቤት ሠራተኞች ከሰኞ እስከ ዓርብ እስከ 11 ሰዓት፣ ቅዳሜ እስከ ሰባት ሰዓት ነው የሚሠሩት እሑድ አና ቅዳሜ ከሰዓት ዕረፍት ናቸው፡፡ መኖርያቸውም ለብቻ ግቢው ውስጥ የተሠራ ቤት ነው፡፡
ያቺ ኢትዮያዊት የቤት እመቤት ሠራተኛዋ ሥራ ስትጨርስ ትጠራትና ወደ አመሻሽ ቡና ይጠጣሉ፡፡ ቅዳሜ ከሰዓትም ባለቤቷ ሳይኖር ትጠራትና አብረው ወሬ እየሰለቁ ቡና ይጠጣሉ፡፡
በወሩ መጨረሻ ለቤት ሠራተኛዋ ደመወዝዋን ለመክፈል ትጠራትና የተነጋገሩትን ደመወዝ ትከፍላታለች፡፡ ይኼኔ ሠራተኛዋ
«የሚቀር ገንዘብ አለኝ» አለች፡፡
«ምን ጠየቀች የቤት እመቤቷ፡፡
«ኦቨር ታይም የሠራሁበት»
«መቼ ምን ሠራሽ»
«በዚህ በዚህ በዚህ ቀን ካንቺ ጋር ቁጭ ብዬ ቡና የጠጣሁበት»
«እንዴ እኔ ብቻ ነኝ እንዴ የጠጣሁት አንቺም ጠጥተሻልኮ»
«ቢሆንም ላንቺ ብዬ እንጂ እኔ ፈልጌ አልጠጣሁም፤ አንቺን ለማዝናናት ነው የተቀመጥኩት እንጂ እኔ ቡና ለመጠጣት መች ከሁለት ደቂቃ በላይ ይፈጅብኛል»
«ወይ አዲስ አበባ ወይ ሀገሬ ሆይ
 ቡና አጣጭ እንደ እናት ይናፍቃል ወይ»
 ሳትል አትቀርም የቤት እመቤቷ፤ ቡና አፍይ ከሚመሰገንበት ሀገር ቡና ለማጣጣት ኦቨር ታይም ወደሚከፈልበት ሀር ስትገባ፡፡ ምንም ማድረግ አልቻለችም፡፡ ሂሳቡን ከፈላ ቡና መጠጣቱን ተወቺው፡፡ ቡና ያለ ሀገሩ ገብቶ እንዲህ መከራውን አየላችሁ፡፡

እግር ያለው ባለ ክንፍ

 ምክንያተ ጽሕፈት ይህንን ጽሑፍ በዚህ ጊዜ እንድጽፍ ምክንያት የሆነኝ ወዳጄ በዕውቀቱ ሥዩም ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ልዩ ልዩ አካላት የሚያቀርቧቸውን ሃሳቦች የሚተነትን አንድ ጥናታዊ ነገር እየሠራሁ ነበር፡፡ በመካከል ሐራሬ እያለሁ በዕውቀቱ «እግር አልባ ባለ ክንፍ» ብሎ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ አንድ ጽሑፍ አወጣ፡፡ የኛ ባህል ሃይማኖታዊ ሳይሆን ተክለ ሃይማኖታዊ ነው፤ ተክለ ሃይማኖታዊ ማለትም በሰማዩ ላይ ያለ ቅጥ በማንጋጠጥ ምድርን ማጣት፣ በዚህም ለድህነት መዳረግ ማለት ነው የሚል ነው ሃሳቡ፡፡   ይህ ጽሑፍ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ታሪክ እና ማንነት የወቅቱ መወያያ እንዲሆን አደረገው፡፡ እኔም ይህንን እንዳዘጋጅ ምክንያት ሆነኝ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ሌሎች አካላት የሚያነሷቸውን ሃሳቦችም ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ የበዕውቀቱን ሃብ ደግሞ ለብቻው፡፡  አቡነ ተክለ ሃይማኖት ማናቸው? አቡነ ተክለ ሃይማኖት በ1186 ዓም በሰሜን ሸዋ ቡልጋ ጽላልሽ ተወለዱ፡፡ አባታቸው የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሲያስተምሯቸው አካባበቢያቸው ደግሞ በዘመኑ የነበሩ ልጆች ይማሩ የነበረውን ፈረስ መጋለብን፣ ቀስት መወርወርን፣ እርሻን እና አደንን አስተምረዋቸዋል፡፡ በሰባት ዓመታቸው ከግብፃዊው አቡነ ቄርሎስ ዲቁናን ከተቀበሉ በኋላ እግዚአብሔር በክህነት ሕዝቡን እንዲያገለግሉ መረጣቸው፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ለክህነት መጠራት በዚህ ዓለም ትዳር መሥርቶ፣ የዓለሙንም ሥራ ሠርቶ መኖር አያስፈልግም ከሚል ፍልስፍና የመነጨ አይደለም፡፡ ከ8ኛው መክዘ ጀምሮ በሀገሪቱ የመንፈስ መቀዛቀዝ ይስተዋል ነበር፡፡ ዮዲት ጉዲት መንግሥቱን ይዛ በክርስትናው ላይ ከዘመተች በኋላ ሰሜኑ እና ደቡቡ ተቆራርጧል፡፡ የሃሳብን ልዕልና የሚያመጣው የመንፈስ ልዕልና ተዳክሟል፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያን የሚዋጅ ኢትዮጵያዊ ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህ ነው የተክለ ሃይማኖት የጥሪ ምክንያት፡፡  አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከአባታቸው ዕረፍት በኋላ ቅስናን ከአቡነ ቄርሎስ ተቀብለው በጽላልሽ አካባቢ በክህነት ከአባታቸው ጋር አገልግለዋል፡፡ አባታቸው ሲያርፉ በወንጌሉ ማንም ሊከተለኝ የሚወድድ ቢኖር  ያለውን ሁሉ ትቶ መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ ያለውን በመከተል ሀብታቸውን ለድኾች መጽውተው ለወንጌል ስብከት ወጡ፡፡ የዋልድባው ገድለ ተክለ ሃይማኖት ወደ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ ከመሄዳቸው በፊት ቅስናን ተቀብለው በሸዋ እና በዳሞት ማገልገላቸውን ይገልጣል፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዳሞት እና በሸዋ ካገለገሉ በኋላ መጀመርያ ደቡብ ወሎ ቦረና ወደ ነበረው ወደ ደብረ ጎል ገዳም ገብተው አሥር ዓመት(12 የሚልም አለ) በትምህርት እና በሥራ አሳልፈዋል፡፡ በዚያም ዋሻ ፈልፍለው አስደናቂ ሕንፃ ሠርተው ነበር፡፡ ገድለ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ እንደሚለው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ ሐይቅ የገቡት በሠላሳ ዓመታቸው ነው፡፡ ይህም የሚያሳየን በሸዋ እና በወላይታ ያገለገሉት ገና በወጣትነታቸው ጊዜ መሆኑን ነው፡፡ በ1216 ዓም አካባቢ ወደ ሐይቅ የገቡት አቡነ ተክለ ሃይማኖት በሐይቅ ከመመንኮሳቸው በፊት ሰባት ዓመት ከመነኮሱም በኋላ ሦስት ዓመት በትም ህርት ፣ በሥራ እና በአገልግሎት ቆይተዋል፡፡ ሐይቅ እስጢፋኖስ በዚያ ዘመን እንደ አዳሪ ትምህርት ቤት ያለ ዩኒቨርሲቲ ነበረ፡፡ ወደዚያ የሚገባ ሁሉ ሦስት ነገሮችን ይማራል፡፡ ትምህርት፣ የጥበበ እድ ሥራ እና ሥርዓተ ምንኩስና፡፡ ትምህርቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን መላ ትምሀርት ያካትታል፡፡ የሞያ ትምህርቱም መጻፍ፣ መደጎስ፣ ሕንፃ ማነጽ፣ ልብስ መሥራት፣ እርሻ፣ የከብት ርባታ እና የሥዕል ሥራን ይመለከታል፡፡ ከእነዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ጽሙድ እንደ ገበሬ ቅኑት እንደ በሬ እንዲሆኑ ሥርዓተ ምንኩስናን ይማራሉ፡፡ በእነዚህ ትምህርቶች የታነፁት መነኮሳት ከገዳሙ ሲወጡ ዛሬ የፒኤች ዲ ተማሪ ዴዘርቴሽን እንደሚያቀርበው የተማ ሩትን ጽፈው አንድ የብራና መጽሐፍ አዘጋጅተው ይወጣሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ሐይቅ ከስምንት መቶ መነኮሳት በላይ በአንድ ጊዜ የሚማሩባት በመጻሕፍትም የበለጸገች ዩኒቨርሲቲ ነበረች፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እዚህ ነው አሥር ዓመታትን ያሳለፉት፡፡ ከሐይቅ ወጥተው በዘመኑ በሥርዓተ ምንኩስና እና በትምህርት ብሎም በጥበበ እድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ወደ ነበረው ወደ ደብረ ዳሞ ሄዱ፡፡ በዚያም ከአቡነ ዮሐኒ ዘንድ መንፈሳዊ ትምህርት፣ ሥርዓተ ምንኩስና እና ጥበበ እድ ሲማሩ ሰባት ዓመት አሳለፉ፡፡ ያነጹት ፍልፍል ድንጋይ ዋሻ፣ መጻሕፍት ሲጽፉ ቀለማቸውን ያስቀምጡባቸው የነበሩትን ሽንቁሮች ዛሬም በደብረ ዳሞ ማየት ይቻላል፡፡ ቀሪዎቹን አምስት ዓመታት ሌሎችን የትግራይ ገዳማት እየተዘዋወሩ ሲመለከቱ ቆይተው ከሸዋ በወጡ በሃያ ሁለት ዓመት እድሜያቸው ሃምሳ ሁለት ሲሆን ለበለጠው ክብር እና ርእይ በግብጽ በኩል ወደ ኢየሩሳሌም ተሻገሩ፡፡ ከኢየሩሳሌም ሲመለሱ በሐይቅ በኩል አድርገው ደብረ ጎልን ተሳልመው በሚዳ እና በመርሐ ቤቴ በኩል ወደ ሸዋ በመምጣት ከዮዲት ዘመን በኋላ በመንፈሳዊ ሕይወት የተጎዳውን ሸዋን እና ደቡብ ኢትዮጵያን በመዘዋወር ለአሥር ዓመታት ያህል አስተምረዋል፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተግተው በማስተማራቸው የተኛው ሁሉ ነቃ፣ የደከመው በረታ፣ የጠፋውም ተገኘ፡፡ በስብከታቸው እንደገና ለነቃው ለመካከለኛው እና ለደቡብ ኢትዮጵያ ሐዋርያትን ለማፍራት እንዲችሉ አንድ ገዳም ለመመሥረትና ደቀ መዛሙርትን ለማስተማር አሰቡ፡፡ እናም ወደ ደብረ አስቦ ገዳም ገቡ፡፡ ቦታውን አስተካክለው እና ከደብረ ዳሞ እና ከሐይቅ የተከተሏቸውን ጥቂት ደቀ መዛሙርት ይዘው በደብረ ሊባኖስ ገዳም ልክ እንደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ሁሉ ሦስቱን ነገሮች ያካተተ አገልግሎት ጀመሩ፡፡ ምንኩስና፣ ትምህርት እና ሥራ፡፡ መነኮሳቱ መንፈሳዊ ትምህርት ይማራሉ፤ በሕገ ገዳም ይመራሉ፤ ለራሳቸው እና ለአካባቢው ሕዝብ ርዳታ የሚሆን እርሻ ያርሳሉ፡፡ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው፣ ገዳማቸውን አደራጅተው፣ ስብከተ ወንጌልንም አስፍተው አስፍተው ሰያደ ላድሉ በሕይወታቸው የመጨረሻ ዓመታት ወደ ደብረ አስቦ ዋሻ ገብተው በአንድ እግራቸው በጾም እና በጸሎት ተወሰኑ፡፡ በጸሎት ብዛትም እግራቸውን በማጣታቸው ስለ ክብራቸው ከእግዚአብሔር ክንፍ ተሰጥቷቸዋል፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አገልግሎታቸውን ፈጽመው ነሐሴ ሃያ አራት ቀን 1287 ዓም በ99 ዓመታቸው ዐረፉ፡፡  ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚነሡ ጥያቄዎች አቡነ ተክለ ሃይማኖት እና የመንግሥት ለውጥ አንዳንዶች «ከዛግዌ ሥርወ መንግሥት ወደ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት የተደረገውን ሽግግር ያከናወኑት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ናቸው፡፡ ይህንንም ያደረጉት ይኩኖ አምላክ የሸዋ ሰው ስለሆነ ለዘራቸው አድልተው ነው» ይላሉ፡፡ በሸዋው ይኩኖ አምላክ እና በዛግዌ ሥርወ መንግሥት ወራሹ በነአኩቶ ለአብ መካከል መቀናቀን የተጀመረው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሐይቅ በትምህርት ላይ በነበሩበት ጊዜ ነበር፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕፃን በነበሩበት ጊዜ ከዳሞት የሚመጣው የሞተለሚያውያን ኃይል ሸዋን ደጋግሞ በመውረር አብያተ ክርስቲያናትን ዘርፏል ሕዝቡንም ማርኳል፡፡ ይህ ጉዳይ የሸዋን ሕዝብ ማስቆጨቱ እና ማነሣሣቱ የማይቀር ነው፡፡ በተለይም ከአኩስም የተሰደደው የሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት ዘር ሸዋ መንዝ ነው የገባው ተብሎ በሚታመንበት ሁኔታ ሸዋዎች ራሳቸውን ለመከላከል መደራጀት ጀምረዋል፡፡ ደቡቡ ኢትዮጵያ ከማዕከላዊው መንግሥት መቀመጫ ከሮሐ እየራቀ ሄዶ ስለነበር ለይኩኖ አምላክ ጥሩ መደላድል ሆኖታል፡፡ ገድለ ኢየሱስ ሞዓ እንደሚተርከው የመንግሥትን ነገር ከይኩኖ አምላክ ጋር የተነጋገሩት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሳይሆኑ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ ናቸው፡፡ ያን ጊዜ ደግሞ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በተማሪነት ሐይቅ ገዳም ውስጥ ነበሩ፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ እና ይኩኖ አምላክ በመንግሥት ጉዳይ ላይ ለመነጋገር የበቁት ይኩኖ አምላክ በሸዋ ላይ ይደርስ ከነበረው የሞተለሚ ጥቃት ሸሽቶ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርት ቤት ወጣትነቱን ያሳለፈ በመሆኑ ነበር፡፡ ሁለቱ ባደረጉት ስምምነት የዐቃቤ ሰዓትነትን መዓርግ ለሐይቅ ገዳም መምህር እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህም ማለት የንጉሡ ገሐዳዊ ግንኙነቶች በዐቃቤ ሰዓቱ በኩል እንዲፈጸሙ ማለት ነው፡፡      የንጉሡ ደብዳቤ ወደ ሐይቅ ገዳም ሲላክ መነኮሳቱ ተቀምጠው እንዲሰሙ     ለገዳሙ የተሰጠውን መሬት የመኳንንቱም ሆነ የነገሥታት ልጆች እንዳይነኩ     ነፍስ የገደለ፣ ንብረት የሰረቀ፣ እግረ ሙቁን ሰብሮ እዚህ ገዳም ገብቶ ቢደውል ከሞት ፍርድ እንዲድን     ለገዳሙ የተሰጠው ርስት ለአገልጋዮች ብቻ ስለሆነ ዘር ቆጥሮ ማንም ተወላጅ እንዳይወርስ     የገዳሙ ርስት መነኩሴ ላልሆነ ጥቁር ርስት እንዳይሰጥ  የሚሉት ታወጁ፡፡ ይህ ሁሉ ሲከናወን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሐይቅ ትምህርት ላይ ነበሩ፡፡ በኋላ ዘመን ይኩኖ አምላክ ኃይሉ እየበረታ ነአኩቶ ለአብም ግዛቱ እየጠበበ እና ኃይሉ እየደከመ ሲሄድ ከወሎ በታች ያለውን ሀገር የያዘው ይኩኖ አምላክ እና ላስታን እና ሰሜኑን የያዘው ይኩኖ አምላክ ለጦር ይፈላለጉ ጀመር፡፡ በዚህ ዘመን ነበር አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከኢየሩሳሌም የተመለሱት፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ያደረጉት ነገር ቢኖር ኃይሉ እየገነነ የመጣውን ይኩኖ አምላክን እና የወቅቱን ንጉሥ ነአኩቶ ለአብን ማደራደር ነበር፡፡ ይኩኖ አምላክ ለመንገሥ ከቅብዐት በቀር የቀረው ኃይል አልነበረም፡፡ የነአኩቶ ለአብ ኃይል ደግሞ ቢዳከምም አልሞተም፡፡ ሁኔታው ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳይሄድ ያሰጋቸው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሁለቱን በማደራደር ከአንድ ስምምነት ላይ አደረሷቸው፡፡      ይኩኖ አምላክ ምንም ኃይል ቢኖረው ነአኩቶ ለአብ እስኪያርፍ ድረስ ንግሥናውን እንዳያውጅ     ከነአኩቶ ለአብም በኋላ የዛግዌ ዘር የላስታን አውራጃ እንዲገዛ     የላስታው ገዥ በፕሮቶኮል ከንጉሡ ቀጥሎ እንዲሆን  ይህ ስምምነት ባይኖር ኖሮ ጦር በሰበሰበው በይኩኖ አምላክ እና ሥልጣን ላይ በነበረው በነአኩቶ ለአብ መካከል በሚፈጠረው ጦርነት የሀገሪቱ ልጆች ባለቁ ነበር፡፡ ዛሬ ቢሆን ይሄ ተግባር የኖቬል ሽልማት የሚያሸልም ነበር፡፡ ይህ ስምምነት በኋላ በዐፄ ይትባረክ ዘመን በመፍረስ የተከሰተውን ጦርነት ያየ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ያደንቃል እንጂ አይተችም፡፡ ሲሦ መንግሥት አንዳንዶች «አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት በዋሉት ውለታ ለቤተ ክርስቲያን ሲሦ መንግሥት ተሰጠ» ይላሉ ይኩኖ አምላክ ሲነግሥ በኢትዮጵያ ውስጥ ጳጳስ አልነበረም፡፡ ከአቡነ ጌርሎስ ሞት በኋላ ከግብፅ የመጣ ጳጳስ አልነበረም፡፡ ይህ ሁኔታ በመንፈሳዊ ትንሣኤ ላይ ለነበረችው ኢትዮጵያ የአገልጋዮች እጥረት አስከተለ፡፡ በዚህ ጊዜ የተሰባሰቡት የኢትዮጵያ ሊቃውንት በትምህርትም በአገልግሎትም የበረቱትን አቡነ ተክለ ሃይማኖትን መረጡ፡፡ የሚሾም ሲኖዶስ አልነበረምና እግዚአብሔር «ሐዋርያትን በሾምኩበት ሥልጣን ሾምኩህ» አላቸው፡፡ ይኩኖ አምላክ ምንም እንኳን በንግሥናው ቢገዛ እንደ ወጉ ሥርዓተ መንግሥት አልተፈጸመለትም ነበር፡፡ በመሆኑም በዘመኑ የነበሩት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥርዓተ መንግሥቱን ፈጸሙለት፡፡ እርሱም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ርስት ሰጠ፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ርስት መስጠት በይኩኖ አምላክ የተጀመረ አይደለም፡፡ እንዲያውም ቅዱስ ላሊበላ ለአኩስም፣ ለላሊበላ፣ ለመርጡለ ማርያም እና ለተድባበ ማርያም የሰጠው ርስት ይበልጣል፡፡ በወቅቱ ለሐዋርያዊ አገልግሎት እና ለተማሪዎች ድርጎ ለቤተ ክርስቲያን ጥሪት ያስፈልጋት ስለነበር ይኩኖ አምላክ ርስት ሰጥቷል፡፡ ይህ ግን ከመንግሥት ዝውውር ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ዛሬም ቢሆን እኮ አንዳንድ የአውሮፓ ሀገሮች ለቤተ ክርስቲያን የተለየ በጀት ይሰጣሉ፡፡ እጨጌ የሚለውን ስም ከርስት አስተዳዳሪነት ጋር የሚያገናኙት ሰዎች አሉ፡፡ እጨጌ የሚለውን ስም ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት የሰጣቸው መንግሥት ሳይሆን የወላይታ ሕዝብ ነው፡፡ በወላይተኛ «ጨጌ» ማለት «ሽማግሌ፣ ታላቅ፣ አባት» ማለት ነው፡፡ ወደ አማርኛ ሲመጣ «እጨጌ» ተባለ፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን አገልግሎት አይቶ ይህንን የሰጣቸው ሕዝቡ ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥልጣን ወዳድ አለመሆናቸውን በግልጽ አሳይተዋል፡፡ ከብዙ ዘመናት በኋላ አቡነ ዮሐንስ 5ኛ ከግብጽ መጥተው አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በግማሽ ኢትዮጵያ በመንበረ ጵጵስና እንዲያገለግሉ ለምነዋቸው ነበር፡፡ እርሳቸው ግን ለሥልጣን ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጸው እንዲያ ሕዝብ ሲወዳቸው እና ሲፈልጋቸው ወደ በኣታቸው ነው የተመለሱት፡፡ «ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሌላ ናቸው »    አንዳንዶች «በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከ8 እስከ 13ኛው መክዘ ባለው ጊዜ የኖሩ ሌላ ተክለ ሃይማኖት የሚባሉ ጻድቅ ነበሩ፡፡ የርሳቸው ታሪክ ከሌላ ተክለ ሃይማኖት ታሪክ ጋር ተዳብሎ አሁን ያለWን ገድለ ተክለ ሃይማኖት አስገኘ፡፡ እናም ጻድቁ ተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ አይደሉም » ይላሉ  እስካሁን ድረስ ይህንን አባባል የሚጠቅሱ ሰዎች ያቀረቡት ማስረጃ የላቸውም፡፡ እገሌ አይቶት ነበር፡፡ እዚህ ገዳም ነበር ከማለት ውጭ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ለሌለ ማስረጃ ሲባል ያለ ማስረጃ አይሰረዝም፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስን በተመለከተ ያሉት ማስረጃዎች አራት ዓይነት ናቸው፡፡      ገድላቸው     የሌሎች ቅዱሳን ገድሎች     ዜና መዋዕሎች እና     የግብፅ ቤተ ክርስቲያን መረጃዎች  ገድለ ተክለ ሃይማኖት እኔ ለማየት የቻልኩት የደብረ ሊባኖስ፣ የሐይቅ እስጢፋኖስ፣ የዋልድባ፣ የጉንዳንዳጉንዲ እንዲሁም ዐፄ ምኒሊክ ወላይታን ሲወጉ ያገኙት የወላይታ ገድለ ተክለ ሃይማኖት ቅጂዎች አልፎ አልፎ ከሚያሳዩት መለያየት በስተቀር የሚተርኩት በ13ኛው መክዘ ስለነበሩት ተክለ ሃይማኖት ነው፡፡ እኒህ ተክለ ሃይማኖት ጽላልሽ ተወልደው፣ በኢትዮጵያ ገዳማት ተምረው፣ በመላ ሀገሪቱ ሰብከው፣ ግብጽ እና ኢየሩሳሌም ተሻግረው፣ ደብረ ሊባኖስን መሥርተው ያገለገሉትን ተክለ ሃይማኖት ነው የሚናገሩት፡፡ ሌላው ቀርቶ ወሎ ጉባ ላፍቶ፣ ጎንደር አዞዞ ተክለ ሃይማኖት የተገኙት ገድላትም ተመሳሳይ ታሪክ ነው የሚተርኩት፡፡ እስካሁን ከኒህኛው ተክለ ሃይማኖት ውጭ ስላሉ ሌላ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚተርክ ገድል አልተገኘም፡፡ አለ ከመባል በቀር፡፡ የኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍትም ሆኑ በአካል ያልተገኙት ማይክሮ ፊልሞቻቸው በተከማቹባቸው በብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ወመዛግብት፣ በመንበረ ፓትርያርክ ሙዝየም እና ቤተ መጻሕፍት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ቤተ መጻሕፍት፣ በብሪቲሽ ሙዝየም እና ቤተ መጻሕፍት፣ በቫቲካን ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት፣ አሜሪካ ኮሌጅቪል በሚገኘው ቅዱስ ዮሐንስ ኮሌጅ ያሉትን ማይክሮ ፊልሞች እና የብራና መጻሕፍት ዝርዝሮችን ብናይ ስለ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ እንጂ ስለ ሌላ ተክለ ሃይማኖት የተጻፈ ገድል የለም፡፡ (የዚህን ዝርዝር የጥናት ውጤት በቅርብ ለኅትመት አበቃዋለሁ፡፡) ሌሎች ገድሎች  ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚያነሡ አያሌ ገድሎች አሉ፡፡ ገድለ አኖሬዎስ ዘሞረት፣ ገድለ አቡነ አኖሬዎስ ዘወረብ፣ ገድለ አቡነ ፊልጶስ፣ ገድለ አቡነ ኤልሳዕ፣ ገድለ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ፣ ገድለ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ፣ ገድለ አቡነ ቀውስጦስ፣ ገድለ አቡነ ማትያስ፣ ገድለ አቡነ ታዴዎስ ዘጽላልሽ፣ ገድለ አቡነ ገብረ ክርስቶስ ዘግድም፣ ገድለ አቡነ መርቆሬዎስ ዘመርሐ ቤቴ፣ ገድለ አቡነ አድኃኒ ዘዳሞት፣ ገድለ አቡነ ኢዮስያስ ዘወጅ፣ ገድለ አቡነ ዮሴፍ ዘእናርያ፣ ገድለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እና ሌሎች ወደ አሥራ ሦስት የሚጠጉ ገድላት ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተጨማሪ መረጃዎች ይሰጣሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ገድላት የሚያነሷቸው ተክለ ሃይማኖት ግን ተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስን ነው፡፡ ዜና መዋዕሎች የይኩኖ አምላክ፣ የዓምደ ጽዮን፣ የዘርዐ ያዕቆብ፣ የሱስንዮስ፣ እና የሌሎቹም ዜና መዋዕሎች ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ ይተርካሉ፡፡ ግብፃውያን መዛግብት የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ቅዱሳን መካከል አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንዱ ናቸው፡፡ እንዲያውም ቤተ ክርስቲያንዋ የአራት ቅዱሳንን ብቻ የልደት በዓል ታከብራለች፡፡ የጌታን፣ የእመቤታችንን፣ የዮሐንስ መጥምቅን እና የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን፡፡ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጥንታውያንም ይሁኑ ዘመናውያን መዛግብት የሚገልጹት በ12ኛው መክዘ ጽላልሽ ተወልደው ስላደጉት ስለ ደብረ ሊባኖሱ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ነው፡፡ እናም ወደፊት አዲስ ነገር ተገኘ ስንባል ያን ጊዜ እንከራከር ካልሆነ በቀር እስካሁን ድረስ ግን ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር የታሪክ ዝምድና ያላቸው ሌላ ተክለ ሃይማኖት መኖራቸውን የሚገልጥ ማስረጃ የለም፡፡ «አቡነ ተክለ ሃይማኖታዊ» ትውልድ በዕውቀቱ ሥዩም ምድርን ትቶ ሰማይ ሰማይን ብቻ ሲመኝ በድህነት የሚዳክር ትውልድን «ተክለ ሃይማኖታዊ» ብሎ ሰይሞታል፡፡ ይህ የበዕውቀቱ ሥያሜ ከሁለት ነገሮች የመጣ ይመስለኛል፡፡ አንደኛው ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ካለ የግንዛቤ ማነስ እና ሁለተኛው ከታሪክ ተፋልሶ የተነሣ፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በሦስት ሥርዓተ ትምህርቶች በተቃኘው የሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርት ቤት የኖሩ ናቸው፡፡ በትምህርት፣ በሥራ እና በምንኩስና፡፡ ሥራ ለዓለማውያን ብቻ ሳይሆን ለመነኮሳትም የግድ አስፈላጊ መሆኑን የተማሩም ያስተማሩም ናቸው፡፡ በተጓዙባቸው ቦታዎች ሁሉ ሦስቱንም ሲያከናውኑ ነው የኖሩት፡፡ በመጨረሻም ወደ ደብረ አስቦ ሲገቡ ገዳማዊው ሥርዓታቸው ትምህርትን፣ ምንኩስናን እና ሥራን ያዋሐደ ነበር፡፡ እናም «ተክለ ሃይማኖታዊ» ማለት «እየሠራ የሚጸልይ፣ እጸለየ የሚሠራ» ማለት እንጂ በሰማዩ ላይ ብቻ ያለ ቅጥ እያንጋጠጡ ምድራዊ ሕይወትን መዘንጋት እና ለድህነት መዳረግ ማለት አይደለም፡፡  እኔ ይህንን ስል ምድራዊ ሕይወት እንደማያስፈልግ የሚያስተምሩ፣ ሥጋ እንዳልተፈጠረ ቆጥረው በሥጋ መኖርን የሚያጣጥሉ የሉም ማለቴ አይደለም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት በሥጋ ተጋብቶ፣ ወልዶ ከብዶ፣ አርሶ ነግዶ፣ ወጥቶ ወረዶ መኖርን የሚያንቋሽሽቱ እና ለነፍስ ብቻ መኖር አለብን የሚሉት ማኔያውያን ተወግዘዋል፡፡ በዕውቀቱ ላነሣው ሃሳብ ትክክለኛ ስያሜውም «ማኔያዊ» እንጂ ተክለ ሃይማኖታዊ አይደለም፡፡ እግር እና ክንፍ በዕውቀቱ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እግራቸውን ያጡት ክንፍ ለማብቀል ሲሉ እንደሆነ አድርጎ ያስቀምጠዋል፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትኮ ክንፍ ያገኙት እግራቸውን ከማጣታቸው በፊት ነው፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ዘንድ አገልግለው ሲፈጽሙ ወደ ምድር በገመድ ወረዱ፡፡ የደብረ ዳሞ መውጫ እና መውረጃው ገመድ ነውና፡፡ ያለፈውን ትጋታቸውን፤ የወደፊቱን አገልግሎታቸውን ያየ ሰይጣን የሚወርዱበትን ገመድ በጠሰባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር አክናፈ ጸጋ ሰጥቷቸው ከተራራው ሥር ሁለት ሺ ክንድ ያህል ርቀው በሰላም ዐረፉ፡፡ ያም ቦታ በኋላ ዘመን በስማቸው ቤተ ክርስቲያን ተተክሎበታል፡፡ እናም ገና ሁለት እግር እያላቸው፤ ተዘዋውረው በሚያስተምሩበት ጊዜ፣ ግብፅ እና ኢየሩሳሌም ከመሄዳቸው በፊት ነው ክንፍ የተሰጣቸው፡፡ ታድያ ሁለት እግር እያላቸው ያገኙትን ክንፍ ለማግኘት እግር ማጣት ለምን ያስፈልጋቸዋል? አቡነ ተክለ ሃይማኖት በአንድ እግራቸው የጸለዩት በቅድመ ጲላጦስ የቆመውን ክርስቶስን በማሰብ እንጂ ክንፍ ለማግኘት ሲሉ አይደለም፡፡ እንደ ወንድሜ እንደ በዕውቀቱ አገላለጥ አቡነ ተክለ ሃይማኖት «እግር አልባ ባለ ክንፍ» ሳይሆኑ «ክንፍ ያለው ባለ እግር ናቸው» አቡነ ተክለ ሃይማኖት በእግር የሚደረስበትን የዘመኑን ቦታ ሁሉ ደርሰውበታል፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ ዙረዋል፡፡ ግብጽ ወርደዋል፤ ኢየሩሳሌም ወጥተዋል፡፡ መንግሥተ እግዚአብሔር ደግሞ በጸጋ ክንፍ እንጂ በእግር አይደረስባትምና ወደ ሰማያዊው ኢየሩሳሌም ሄደው እንዲያዩ አስቀድሞ የሰጣቸውን ክነፍ እግራ ቸው በተቆረጠ ጊዜ ገልጦላቸዋል፡፡ ያንጊዜም በእግር ወደማይደረስበት ሰማያዊ መቅደስ ገብተው ከሱራፌል ጋር አጥነዋል፡፡ በእግር የሚደረስበትን ለፈጸመ ሰው ከክንፍ ውጭ ምን ሊሰጠው ኖሯል? በእንተ በዕውቀቱ ሥዩም ሀገራዊ መንፈስ ፍለጋ በዕውቀቱ ሥዩም ነገሮችን በአዲስ መልክ ከሚያዩ ጥቂት የሀገራችን ጸሐፍት አንዱ ነው፡፡ ገና ብዙ ሥራ የሚጠበቅበት ወጣት ጸሐፊም ነው፡፡ ሕይወቱን ለጽሑፍ የቀየደ ሰውም ነው፡ እኔ በዕውቀቱ ሥዩም ይህንን ጽሑፍ ሲጽፍ ዓላማው ቤተ ክርስቲያንን መፃረር ነው ብዬ ኣላምንም፡፡ በጽሑፉ መግቢያ እንደገለጠው ነባሩን ባህል በዓለማዊ መነጽር ማየት እፈልጋለሁ ነው ያለው፡፡ ይህም ማለት የእስላሙንም የክርስቲያኑነም፣ ሃይማኖታዊውንም ሃይማኖታዊ ያልሆነውንም ነባር ባህል በ «ዓለማዊ´E መነጽር ሊያይ ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ አንድን ነገር በፈለገው መንገድ ማየት የተፈጽሮ መብቱ ነው፡፡ በዚህ አንከራከረም፡፡ በዕውቀቱ እንደዚህ ያለ ነባር፣ ሕዝብ የተቀበለውን እና መከራከርያ ያለውን ነገር ሲያይ እንደሌላው ነገር በሳቅ በሥላቅ፣ በቀልድ፣ በእግረ መንገድ ባያደርገው ግን እመርጣለሁ፡፡ ካነሣ ጠንካራ መከራከርያ አንሥቶ መሞገት ነው ያለበት፡፡ በአሁኑ ጽሑፉ ግን ይህንን አላየሁበትም፡፡ በዕውቀቱ እንደሚለው ለርሱ ዋናው ሃሳቡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ መከራከር ሳይሆን በአቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድ ነቁጥ ታሪክ እንደርሱ አገላለጥ «እግር አጥተው ክንፍ ባወጡበት» ታሪክ ተምሳሌትነት የሕዝቡን ነባር ሁኔታ ማየት ነው፡፡ ይህም ቢሆን ግን ሕዝቡ ለሌላ ነገር ሲጠቀምበት የኖረውን ስያሜ አንሥቶ ምንም ዓይነት በቂ መከራከርያ ሳያቀርብበት ለሌላ ነገር ከሚጠቀም ይልቅ ሌላ ስያሜ ቢጠቀም የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ «ተክለ ሃይማኖታዊ» የሚለው ማሳያ ከእውነታው ውጭ ቀርቧልና፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዕውቀቱን አደንቀዋለሁ፡፡ ብዙ ጸሐፊዎች ከውጭ በመጣ ሃሳብ ኢትዮጵያን ማየት ሲመርጡ በሀገራዊ ተምሳሌት እና ሃሳብ ራሳችንን ለማየት መሞከሩ በዕውቀቱ ውርጅናሌውን የያዘ ጸሐፊ ነው እንድልም አድርጎኛል፡፡ ምንም እንኳን «ተክለ ሃይማኖታዊ» ብሎ በሰጠው ሥያሜ ትርጉም ባልስማማም ሀገርኛ ስያሜ እና ተምሳሌት ለመምረጥ መጣሩን ግን አደንቃለሁ፡፡ በ1956 ዓም «የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ» የምትል ትንሽ፣ ግን እጅግ ጠቃሚ መጽሐፍ ያሳተሙት እጓለ ገብረ ዮሐንስ የኢትዮጵያን ሥልጣኔ «ያሬዳዊ ሥልጣኔ» ብለው ሰይመውት ነበር፡፡ «ከሥጋ መንፈስ ይበልጣል፣ ሥጋዊ ሕይወት ወደ መንፈሳዊ ሕይወት ተመስጦ ማደግ አለበት፣ የመጨረሻው ደረጃ መንፈሳዊ አድናቆት እና ከኃይላተ ሰማይ ጋር መተባበር ነው» በሚል ዘይቤ የተቃኘ ሥልጣኔ ነው ይላሉ፡፡ እርሳቸውና በዕውቀቱን የሚያመሳስላቸው ሁለቱም ሀገራዊ ስያሜ እና መንፈስ ፍለጋ መኳተናቸው ነው፡፡ ኦርቶዶክስነት ለእኔ ኦርቶዶክስነት ሃይማኖት ብቻ አይደለም፡፡ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሀገሪቱ ውስጥ ከነበራት የእምነት፣ የታሪክ፣ የባህል፣ የሥልጣኔ፣ የትምህርት እና የሥነ መንግሥት ድርሻ አንፃር በሀገሪቱ ሕዝቦች ውስጥ እንደ ድር እና ማግ የተያያዙ ነገሮች አሏት፡፡ እንደ እኔ ግምት ሁለት ዓይነት ኦርቶዶክሶች አሉ፡፡ የሚያምኑ ኦርቶዶክሶች እና የማያምኑ ኦርቶዶክሶች፡፡ የሚያምኑት ኦርቶዶክሶች ኦርቶዶክስን የድኅነት መንገድ አድረገው የሚቀበሏት ናቸው፡፡ ዶግማዋ፣ ሥርዓቷ፣ ትውፊቷ የሚመራቸው ናቸው፡፡ የማያምኑት ደግሞ ባህልዋ፣ ፍልስፍናዋ፣ ሥርዓተ ኑሮዋ፣ ታሪኳ፣ ሥነ ምግባርዋ እና ሀገራዊ እሴ ቷን በማወቅም ባለማወቅም የተቀበሉት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ፕሮቴስታንት፣ ካቶሊክ፣ ባህላዊ እምነት አማኝ፣ እምነት የለሽ፣ ሙስሊም፣ ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በባህላቸው፣ በአስተ ሳሰባቸው፣ በታሪካቸው፣ በመሠረታቸው፣ በሥነ ምግባር እሴታቸው፣ በይትበሃላቸው እና በሀገራዊ ስሜታቸው ግን ኦርቶዶክሶች ናቸው፡፡ በተለያየ የክርስትና ባህሎች ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን እንስሳው ሁሉ ተቀድሷል እያሉ ሲያስተምሩ ቢሰሙም አይጥ እና ጉርጥ ሲበሉ፣ ወይንም ፈረስ እና አህያ አርደው ሠርግ ሲደግሱ ግን አልታዩም፡፡ በዕውቀቱ ከሁለተኛዎቹ ኦርቶዶክሶች የሚመደብ ይመስለኛል፡፡ በተደጋጋሚ እንደ ሚለው «እኔ በራሴ ትርጉም ኦርቶዶክስ ነኝ፤ የግድ እንደ እናንተ አድርጌ ማመን ግን አይጠበቅብኝም» ይህ አባባሉ ነው ከሁለተኞቹ እንድመድበው ያደረገኝ፡፡ በተደጋጋሚ ገድላቱን እና ትርጓሜያቱን ሲያነብብ እና ሲጠቅስ አየዋለሁ፡፡ ለሀገራዊ እሴቶች ዋጋ ይሰጣል፡፡ ቋንቋው «ኦርቶዶክሳዊ» ነው፡፡ የሥነ ምግባር መመሪያዎቹም እንዲሁ፡፡ በዐሉላ ቋንቋ በዕውቀቱ «ሲቪክ ኦርቶዶክስ» ነው፡፡ በዕውቀቱን የመረጠውን ሃሳብ እንዲወክልለት «ተክለ ሃይማኖታዊ» የሚለውን ቃል እንዲጠቀም ያደረገው ፀረ ቤተ ክርስቲያን ስለሆነ ሳይሆን ሲቪክ ኦርቶዶክስነቱ አይሎበት ነው ባይ ነኝ፡፡ ምንም እንኳን የትርጉም ስሕተት ቢፈጥር፡፡ አሉታዊ ጥቅም ሃይማኖት ማኅበረሰቡ የሚቀበለውና የሕይወት ሥርዓት ሆኖ የሚቀጥል ነገር ነው፡፡ እናም በማኅበረሰቡ ውስጥ ይሰርጽና ዘወትራዊ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ በመካከል ጥያቄ የሚጠይቁ፣ የተለየ ሃሳብ የሚያቀርቡ እና የሚሞግቱ ሲመጡ ግን ሃይማኖታዊ ጉዞ ከተለምዶአዊነት ወጥቶ ንቅናቄያዊ ይሆናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍቷን በቀኖና እንድትወስን፣ ሥርዓቷን እንድትወስን፣ የሃይማኖት መግለጫዋን ወስና እንድታወጣ፣ ሕግ እና ደንብ እንድትሠራ፣ መጻሕፍትን እንድትጽፍ፣ ያደረጓት እነዚህን መሰል ተግዳሮቶች በየዘመናቱ መኖራቸው ነው፡፡ ሄሊቪዲየስ ተነሥቶ በቅድስት ድንግል ማርያም ላይ የተለየ ትምህርት ባያመጣ ኖሮ አባ ጄሮም እና አባ ኤጲፋንዮስ የጻፏቸውን መጻሕፍት ባላገኘን ነበር፡፡ ቴዎድሮስ የተባለ የጦር አዛዥ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫን ስለ ሃይማኖት ባይገዳደረው ኖሮ አስደናቂውን ርቱዐ ሃይማኖት የተሰኘ መጽሐፍ ባላገኘን ነበር፡፡ የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዜና መዋዕል እንደሚነግረንም «በንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን በሃይማኖት ምክንያት ክርክር ሆነ፡፡ አባ ጊዮርጊስም ከአንድ ፈረንጅ ጋር ተከራክሮ ረታው፡፡ መጽሐፈ ምሥጢርንም ደረሰ» መልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬ ያንን የመሰለ ኮኩሐ ሃይማኖት የተሰኘ መጽሐፍ እንዲጽፉ ምክንያት የሆናቸው አባ አየለ ተክለ ሃይማኖት የሚባል ካቶሊካዊ ስለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የጻፈው ጽሑፍ ነው፡፡ እርሳቸው ባረፉ ጊዜ ይኼው ሰው እያለቀሰ መጣ አሉ፡፡ ዘመዶቻቸው ተናድደው «ደግሞ እንዴት ታለቅሳለህ?» ብለው ቢጠይቁት «እንኳንም ጻፍኩ፤ እኔ ባልጽፍ እኒህን የመሰሉ ሊቅ ገንዛችሁ ልትቀብሯቸው ነበርኮ፡፡ እኔ በመጻፌ እርሳቸውም ጻፉ፤ ምነዉ ደጋግሜ በጻፍኲ ኖሮ» አለ ይባላል፡፡ እነ አስረስ የኔ ሰው ያንን የመሰለ «ትቤ አኩስም መኑ አንተ» የተሰኘ የታሪክ፣ የእምነት፣ የቅርስ እና የሥነ ልሳን መጽሐፍ የጻፉት በወቅቱ ለተነሡት የታሪክ፣ የቋንቋ እና የእምነት ተግዳሮቶች መልስ ለመስጠት ነው፡፡ እናም የበዕውቀቱ ጽሑፍ በዚህ ረገድ ከታየ ያለንን ይበልጥ ለመግለጥ እና ይበልጥ ለማብራራት ዕድል የሚከፍት አሉታዊ ጠቀሜታ አለው ብዬም አስባለሁ፡፡ እንደነ መንግሥተ አብ ያሉ ጸሐፍትም ከእምነት ነጻነት እና ከሃሳብ ነጻነት የቱ ይበልጣል? የሚል መከራከርያ ይዘው እንዲነሡም አድርጓል፡፡ የበዕውቀቱ ጽሑፍ እና የመጻፍ ነጻነት በምንም መንገድ ይሁን በምንም እንደ በዕውቀቱ ያሉ ጸሐፍት የመጻፍ ነጻነታቸው መከበር አለበት፡፡ ጥያቄ ያለው ወይንም በሃሳባቸው የማይስማማ ሰው እስከ ሕግ አግባብ ድረስ በመሄድ ጤናማውን እና የሠለጠነውን መንገድ ተከትሎ ይሞግታል፡፡  አንድ ጸሐፊ በመጻፉ ምክንያት ብቻ አካላዊም፣ ሃሳባዊም ጥቃት እንዳይደርስበት የምንከላከለው በሚጽፈው ሃሳብ ስለምንስማማ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ለማንስማማበትም ሃሳብ ነጻነት መሟገት አለብን፡፡ ሃሳቡን እየተከራከርነውም፤ መብታችን ተደፍሯል ብለን በፍርድ ቤት እየከሰስነውም ቢሆን ለሃሳብ ነጻነቱ ግን መሟገት ግድ ይለናል፡፡  በርግጥ ልጁ ይህንን ተግባር እንደ ዓላማ የያዘ ልጅ አለመሆኑን ከጓደኞቹም ከራሱም አረጋግጫለሁ፡፡ በዕውቀቱን ይቅርታ ጠይቋል፡፡ በዕውቀቱም ይቅር ብሏል፡፡ በሃሳቡ ባይስማማም ባደረገው ነገር ግን መፀፀቱን ገልጧል፡፡ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ሚዲያዎች ሁኔታውን ያራገቡበት መንገድ ግን ነገሩ አሁንም የቀጠለ እና ሌላ አደጋ ያለ በሚያስመስል መልኩ ነው፡፡  እናም በዕወቀቱ ይጻፍ፣ የማልስማማበትንም ነገር ይጻፍ፣ እኔም የምስማማበትን እይዛለሁ፣ የማልስማማበትን እሞግታለሁ፡፡ ለበዕውቀቱ የመጻፍ ነጻነት ግን ጥA፡

Monday, August 15, 2011

ጰራቅሊጦስ




 
 
በዓለ ጰራቅሊጦስ ወይም በዓለ ጰንጠቆስጤ ከዘጠኙ የጌታችን ዐበይት በአላት አንዱ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የወረደበትን ቀን የምናስብበት በዓል ነው። ጰራቅሊጦስ የግሪክ ቃል የሆነ የመንፈስ ቅዱስ መጠሪያ ነው። ትርጉሙም በጐን የሚቆም፣ የሚረዳ፣ የሚያጽናና ማለት ነው። አበው መንጽሂ /የሚያነጻ፣ የሚቀድስ/ መጽንሂ /የሚያጸና፣ የሚያበረታ/ በማለት ይገልጹታል። ጰንጠቆስጤ የሚለውም የግሪክ ቃል ሲሆን “ፔንዲኮንዳ” ሃምሳ “ፔንዲኮስቲ” ሃምሳኛ ማለት ነው። በዓሉ ጌታችን ባረገ በአሥረኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ በተነሳ በሃምሳኛው ቀን ይከበራል።

የበዓሉ የትመጣ
 
እስራኤል ከግብጽ ከወጡና ሕገ ኦሪት ከተሰጠቻቸው ጊዜ ጀምረው በዓለ ፋሲካን ለማክበር በኢየሩሳሌም ይሰበሰባሉ። ፋሲካ ለእስራኤል የነፃነት በዓላቸው ስለሆነ በስደት ምክንያት ወደ ተለያዩ ሀገሮች ከተበተኑ በኋላም እንኳን ካሉበት በመምጣት በዓሉን የሚያከብሩ ሲሆን ከፋሲካ ማግስት ጀምረው ሃምሳውን ቀን በዓል አድርገው አገር የቀረበው በየአገሩ እየሄደ አገር የራቀበት ስንቁን ይዞ ከዚያው ከኢየሩሳሌም ይሰነብታል። በሃምሳኛው ቀን በዘፀ ፴፬፥፳፪፣ በዘሌዋ ፳፫፥፲-፲፯ በታዘዙት መሠረት በዓለ ሰዊትን /የእሸት በዓልን/ ካመረቱት ምርት በኩራቱን ለመሥዋዕት በማቅረብ ያከብራሉ። በዓለ ፋሲካን ለማክበር ከዝርወት ተሰብስበው የነበሩ አይሁድ ሁሉ ወደየመጡበት የሚመለሱት ይህን በዓለ ሰዊትን ካከበሩ በኋላ ነው። በዓለ ሰዊትን በዝርወት የተሰበሰቡና በዚያውም የሚኖሩ አይሁድ አብዛኛውን ጊዜ በዓል የሚያከብሩት በደብረ ጽዮን ነው።
 
በዚሁ ልማድና ሥርዓት መሠረት ጌታችን በመሥቀል ተሰቅሎ ድኅነተ ዓለምን በፈጸመበት ዓመት እስራኤላዊያን በዚች በደብረ ጽዮን በዓለ ሰዊትን ለማክበር ተሰብስበው እንዳሉ ሐዋርያት ደግሞ ጌታችን የነገራቸውን ተስፋ እየተጠባበቁ በዚሁ በደብረ ጽዮን በቅዱስ ማርቆስ እናት ቤት ውስጥ ተሰብስበው ነበር። ይህች ቀን ጌታ ባረገ አሥረኛው ቀን ነበረች። በዚህች ዕለት ጠዋት አይሁድ የቀድሞውን በዓል ሲያከብሩ ለሐዋርያት ጌታ የነገራቸው የተስፋ ቃል ተፈጸመላቸው፤ መንፈስ ቅዱስ ተሰጣቸው /ሐዋ ፪፥፩-፬/ በማለት በሐዋርያት ሥራ ላይ ጽፎልናል። ስለዚህም ቅዱሳን ሐዋርያት በዲድስቅሊያ 31 “ከዕርገቱ ቀን በኋላ ታላቅ በዓል ይደረግ፤ በዚህች ቀን በሦስተኛው ሰዓት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጰራቅሊጦስን ልኮልናልና እኛም በእርሱ ስጦታዎች ተሞላን አዳዲስ ቋንቋን ተናገርን” በማለት በዓሉን በቤተ ክርስቲያን እንድናከብር ሥርዓትን ሠርተዋል። በዚህም መሠረት በነቢያትና በሐዋርያት ትምህርት ላይ የታነጸችው ቤተ ክርስቲያናችንም ይህንኑ በዓል ዛሬም ድረስ ታከብራለች።      
 
 
ትንቢት
 
በቅዱስ መጽሐፍ ስለ መንፈስ ቅዱስ የተገለጠውን ስናይ የአብና የወልድ ሕይወታቸው የሆነ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለዓለሙ ሁሉ ሕይወትን የሚያድል ስለሆነ ምሉዕ ሆኖ በሁሉ ቦታ እንዳለ “የእግዚአብሔርም መንፈስ በውሃ ላይ ሰፍፎ ነበር´’ /ዘፍ ፩፥፪/ በማለት ይገልጻል። ይህ የእግዚአብሔር መንፈስ በዘመናት ሁሉ ከእግዚአብሔር ወዳጆች ጋር በመሆን ምግባር ትሩፋት እንዲሠሩ ያደርጋል። ሆኖም ግን የሰው ልጆች ኃጢአትን በሰሩ ጊዜ በዓለም ላይ ምሉዕ የነበረው የእግዚአብሔር መንፈስ ከሰው እንደራቀ ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይገልጽልናል። እግዚአብሔርም መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፥ እርሱ ሥጋ ነውና፤ ዘመኖቹም መቶ ሃያ ዓመት ይሆናሉ አለ /ዘፍ ፮፥፫/። ኋላም ሰውን ወዳጅ የሆነው ልዑል አምላካችን የሰውን ልጅ በሞቱ ሊያድነውና በቅዱስ መንፈሱም ሊያጸናውና ሊያጽናናው መፍቀዱን በነቢያት አድሮ ትንቢት አናግሯል። ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ “ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል። ከሥሩም ቁጥቋጥ ያፈራል። የእግዚአብሔር መንፈስ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ የምክርና የኃይል መንፈስ የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።” /ኢሳ ፲፩፥፪/ በማለት ተናግሯል። በተለይም የመንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት መውረድ “መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢትን ይናገራሉ፥ ሽማግሌዎችሁም ሕልምን ያልማሉ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ…” /ኢዩ ፪፥፳፰/ የሚል የነቢይ ቃል ነበረ።
 
ትንቢቱጻሜ
 
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ የመረጣቸው ደቀ መዛሙርት በመጀመሪያ አካባቢ ይከተሉት የነበረው ምድራዊ ሹመትና ሥልጣን ከመፈለግ አንጻር ነበረ። ይሁን እንጂ እየዋሉ እያደሩ ቃሉን ሲሰሙ ለምድራዊ ክብር ሳይሆን ለሰማያዊ ክብር መጠራታቸውን ነግሯቸዋል። ይሁን እንጂ ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣበትን የሰውን ልጅ ከዘላለማዊ ሞት የማዳን ዋነኛ ዓላማ ለመፈጸም ተቃርቦ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ደቀ መዛሙርቱ የፍርሃትና የመታወክ ልብ ነበራቸው። ይህ የሚታወክ ልቦና ሊረጋጋ የሚችለው በሚኖራቸው ፍጹም እምነት እንደሆነ ለማስረገጥ “ልባችሁ አይታወክ በእግዚአብሔር እመኑ በእኔ ደግሞ እመኑ” /ሐዋ ፲፬፥፩/ ብሏቸዋል። ፍጹም የሆነ እምነት ያለው ሰው አይረበሽም አይታወክም። የሚያስፈራው የሚያስደነግጠው ነገር አይኖረውም።
 
ጌታ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ደቀ መዛሙርቱን “ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ” /ሉቃ ፳፬፥፵፱/ ባላቸው መሠረት የተገባላቸውን ቃል ኪዳን በተስፋ ሲጠብቁ ቆይተዋል። ይህ ኃይል መንፈሳዊና ሰማያዊ ኃይል ነው ይህም የሚገኘው ከእግዚአብሔር ብቻ ነው። ይህንን ኃይል ለማግኘት እግዚአብሔርን በትዕግስት ሆኖ ደጅ መጥናት ያስፈልግ ነበረ። ስለዚህም ደቀ መዛሙርቱ “ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው ሳሉ ድንገት እንደሚነጥቅ ዐውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ፣ ተቀምጠው የነበረበትን ቤት ሞላው እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው በእያንዳንዳቸው ላይ ተቀመጡባቸው በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር” እንዲል /ሐዋ ፪፥፪-፬/። ሁሉም በአንድ ልብ ነበሩ፤ የተከፋፈለ ሃሳብ አልነበራቸውም። ዛሬ የብዙዎቻችን ልብ ቀርቶ የእያንዳንዳችን ልብ እንኳን አንድ አይደለም። በብዙ ነገር ልቦናችን ይከፋፈላል። እግዚአብሔር ኅብረትና ፍቅር ከሌላቸው ሰዎች ጋር ምንም አይሠራም።
 
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ “አብ በስሜ የሚልክው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው ኣጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል። እኔም የነገርኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።” /ዮሐ ፲፬፥፳፮/ ባለው መሠረት ደቀ መዛሙርቱን የሚያጽናና፣ የሚያረጋጋና ምሥጢርን የሚገልጽ ጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስን ልኮላቸዋል። ደቀ መዛሙርቱ ይህንን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ በበዓለ ሃምሳ ካገኙበት ጊዜ ጀምሮ የተሰጣቸውን የምሥራች የሆነውን ወንጌል ለፍጥረት ሁሉ ለመስበክና ኃላፊነታቸውን በሚገባ ለመወጣት ራሳቸውን ለእግዚኣብሔር የተቀደሰ አድርገው አቅርበዋል። በዚሁ ዕለት መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ከወረደላቸውና የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ከሆኑ በኋላ በመንፈስ ብርቱ ሆነዋል፣ በዕውቀት ጎልምሰዋል፣ ከብልየት ታድሰዋል።
 
በዕለቱ ከተለያዩ የዓለም አገራት በዓለ ሃምሳ የተባለውን ታላቅ በዓል ለማክበር ኢየሩሳሌም የተሰበሰቡ ብዛት ያለው ሕዝብ ሐዋርያት በቋንቋቸው ወንጌልን ሲሰብኩ በመስማታቸው ተደንቀዋል። “እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋቸው ሲናገሩ ይሰማ ስለነበር የሚሉትን አጡ ተገርመው ተደንቀውም እንዲህ አሉ፥ እነሆ እነዚህ ሁሉ የሚናገሩ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን” /ሐዋ ፪፥፯-፰/ በማለት በመገረም ይናገሩ ነበር። በዚህ ዕለት ቅዱስ ጴጥሮስ በሕዝቡ መሐል ተገኝቶ አይሁድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት አድርገው መከራ እንዳጸኑበት፣ በመስቀል ላይ እንደሰቀሉት፣ እንደገደሉት እርሱ ግን ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ እኛ ደግሞ ለዚህ ምስክሮች ነን ብሎ ማንንም ሳያፍርና ሳይፈራ ያስተምር ነበር። ባስተማረው ትምህርት ልባቸው የተነካ ብዛት ያላቸው ሰዎች ሐዋርያትን ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ ሲሉ ጠይቀዋል። ቅዱስ ጴጥሮስ “ንስሐ ግቡ ኃጢያታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ” በማለት ንስሐ እንዲገቡና የተስፋው ቃል ተሳታፊዎች እንዲሆኑ አስተምሯቸዋል።
 
ቃሉን ሰምተው ንስሐ የገቡና የተጠመቁ ሰዎች ቁጥራቸው ሦስት ሺህ ያህሉ ነበር። ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፥ በዚያን ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ፤ በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቁረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር። /ሐዋ ፪፥፵፩-፵፪/። ያመኑት ሁሉ አብረው በኅብረት ይኖሩ ነበር ያላቸውን ሀብት ንብረት ሳይቀር አንድ ላይ አደረጉ። በመካከላቸው መለያየት አልነበረም። ሀብታም ደሃ ትንሽ ትልቅ የሚል ልዩነት አልነበረም። ሁሉም እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ ነበሩ። ሁለት ሦስት ሆናችሁ በስሜ በምትሰበሰቡበት በመካከላችሁ እገኛለሁ ብሎ ነበረና በስሙ አንድ ሆነው በፍቅር በመገኘታቸው “ስጦታን ለሰው ልጅ ሰጠህ” /መዝ ፷፯፥፲፰/ የሚለው የዳዊት ቃል በእነርሱ ላይ ተፈጽሟል። ሰማያዊ በረከትንና ጸጋውን ሊቀበሉ ችለዋል። በዚህም ስጦታ የመንፈስ ልዕለናን ይዘው ጨለማውን ዓለም በወንጌል አብርተዋል። ኃይለ አጋንንትን ድል አድርገዋል። አላውያን ነገሥታትን አሳፍረዋል።
 
ቤተ ክርስቲያን በዚህ ቀን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታለች። ልጆች የሆንን ሁላችንም በአርባና በሰማንያ ቀን ስንጠመቅ ነው ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማሕፀነ ዮርዳኖስ የተወለድነውና ከሥላሴ ልጅነት ያገኝነው። ይህን በጥምቀት ጊዜ ያገኘነውን ጸጋ አክብረን ልንይዘው ይገባናል። “በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግስትም እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሱ በሰላም ማሰማሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ” /ኤፌ ፬፥፪-፫/ እንዲል እንደተሰጠን የጸጋ ስጦታ መጠን ቤተ ክርስቲያንን በፍቅር በአንድነት ሆነን ልናገለግል ይገባናል። እርሱ በማይታበለው ቃሉ ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም ያለ ጌታ ዛሬም በደሙ የዋጃትን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆችን አይተዋቸውም። ብቻ እኛ በቤቱ ጸንተን በፍቅር እንኑር። ሁሌም እርሱ ከእኛ ጋር ይኖራል። ለዚህም የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጸጋ የእመቤታችን ኣማላጅነት የሐዋርያት ረድኤት በረከት አይለየን። አሜን!
 
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወዳጄ ሆይ ተነሽ፣ ውበቴ ሆይ ነይ




ብዙውን ጊዜ “ጠቢቡ” የሚለው ቃል ይቀጸልለታል። በእርግጥም በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ንጉሥ ሆኖ በተሾመ ጊዜ በፍጹም አትኅቶ (ራስን ዝቅ በማድረግ) “መልካሙንና ክፉውን ይለይ ዘንድ ለባሪያህ አስተዋይ ልቡናን ስጠው” በማለት ከብርና ከወርቅ ይልቅ የበለጠውን ነገር በመለመኑ እግዚአብሔር ተደሰተበት። “እኔ እንደቃልህ አድርጌልሀለሁ እነሆ ማንም የሚመስልህ ከአንተ በፊት እንደሌለ ከአንተም በኋላ እንዳይነሳ አድርጌ ጥበበኛና አስተዋይ ልቡና ሰጥቼሀለሁ” ተባለ። /፩ ነገ. ፫፥፱-፲፬/ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከ፲፻፲፱-፱፻፸፱ ዓ.ዓ. የነገሠው ሰሎሞን።

ሰሎሞን እጅግ በጣም በጥበብና ልብን በሚነኩ ምሳሌዎች የተሞሉ አምስት መጻሕፍትን ደርሷል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ “መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን” ይባላል። ከመዝሙራት ሁሉ የሚበልጥ መዝሙር እንደማለት ነው። በዚህ መጽሐፍ እግዚአብሔር አምላካችን በገለጠለት መጠን በሴት አንቀጽ እየጠራና በፍቅር እየመሰለ ስለሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያንና ስለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ብዙ ምሥጢር ተናግሮበታል።

ስለድንግልናዋ “እኅቴ ሙሽራ የተቆለፈ ገነት፣ የተዘጋ ምንጭ፣ የታተመ ፈሳሽ ናት።” /መኃ. ፬፥፲፪/። ስለስደቷ ደግሞ “አንቺ ሱለማጢስ ሆይ ተመለሽ፣ ተመልሽ፣ እናይሽ ዘንድ ተመለሽ፣ ተመለሽ።” ይላታል /መኃ. ፯፥፩/። በዚያም ሳያበቃ ስለእረፍቷና ትንሣኤዋ ደግሞ “ውዴ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፤ ወዳጄ ሆይ ተነሽ፣ ውበቴ ሆይ ነይ።” በማለት ይናገራል /መኃ. ፪፥፲/። ይህንን ቃል ግዕዙ እንዲህ ይለዋል “ያውሥእ ወልድ እኁየ ወይብለኒ ተንሥኢ ርግብየ ወንዒ ሠናይትየ።” ልጅ ወንድሜ ወልድ /እግዚአብሔር/ እንዲህ አለኝ። ወዳጄ /ርግቤ/ ሆይ ተነሽ፣ ውበቴ ሆይ ነይ። “ውዴ” የተባለ ወልድ፤ የአብ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንድያ ልጁ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” እንዳለ /ማቴ. ፫፥፲፯/።

ወዳጄ፣ ውበቴ የተባለች ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። የሰው ልጅ በሰይጣን አሽክላ ተተብትቦ በነበረበት የጨለማ ዘመን ለሰው ልጆች ብርሃን ክርስቶስን ያስገኘች በመሆኗ እንደዚሁም ቅድመ ዓለም ያለ እናት የተወለደ ቃለ አብ፤ ድኅረ ዓለም ያለ አባት ሲወለድ ለእናትነት የተመረጠች፣ ስደቱን የተሰደደች፣ በአጠቃላይ በመዋዕለ ሥጋዌው ከአጠገቡ ያልተለየች በመሆኗ “ወዳጄ” ይላታል።

ውበቴ መባሏም ስለብዙ ምክንያት ነው። አስቀድሞ አባቷ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “ልጄ ሆይ ስሚ፣ እይ፣ ጆሮሽንም አዘንብይ፣ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ ንጉሥ ውበትሽን ወድዷልና እርሱ ጌታሽ ነውና።” በማለት እንደተናገረ /መዝ. ፵፬፥፲/ እመቤታችን በውስጥ በአፍአ፣ በነቢብ በገቢር፣ ፍጹም እንከን የሌለባት፤ ድንጋሌ ሥጋን ከድንጋሌ ነፍስ አስተባብራ የተገኘች፤ በነፍስ፣ በሥጋ፣ በልቡና ንጽሕት፣ ቅድስት በመሆኗ ነው። ቅዱስ ኤፍሬም በረቡዕ ውዳሴው ላይ “አብ በሰማይ አይቶ እንደ አንቺ ያለ አላገኘምና፤ አንድ ልጁን ላከው፣ በአንቺም ሰው ሆነ።” በማለቱ አንስት በሙሉ መርገመ ሔዋን ይተላለፍባቸው ነበርና ለአምላክ እናት የምትሆን ሴት በጠፋችበት እርሷ መገኝቷን ያመለክታል። በተመሳሳይ መልኩም ይህን ሃሳብ ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው እንዲህ በማለት ያጠነክረዋል። “እግዚአብሔር አብ በሰማይ ሆኖ ምሥራቅንና ምዕራብን፣ ሰሜንና ደቡብን፣ ዳርቻዎችንም በእውነት ተመለከተ፤ ተነፈሰ፣ አሻተተም እንደ አንቺ ያለ አላገኘም፤ የአንቺን መዐዛ ወደደ የሚወደውን ልጁን ወደ አንቺ ላከ።” እንግዲህ እመቤታችን “ውበቴ” መባሏ በእንደዚህ ያለው ምክንያት መሆኑን ማወቅ ይገባል።

እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር ሦስት ዓመት ከቤተሰቧ ጋር፣ አሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ፣ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀናት ጌታን ጸንሳ፣ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታችን ጋር፣ አሥራ አምስት ዓመት በወንጌላዊው ዮሐንስ ቤት ከኖረች በኋላ በስድሳ አራት ዓመቷ ጥር ፳፩ ቀን በ፵፱ ዓ.ም. አርፋለች። /ነገረ ማርያም/

የሰማዕታት እናታቸው፣ የሐዋርያት ሞገሳቸው፣ የነቢያት ትንቢታቸው፣ እግዝእተ ብዙኃን ድንግል ማርያም፤ አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ኃይል አርያማዊት /ከሰማይ የወረደች ኃይል/ አይደለችም። ሰው ሆና ከአዳም ዘር የተወለደች እንጂ። ለዚህም ልደቷና እድገቷ ብቻ ሳይሆን እረፍቷም አሳማኝ ምስክር ነው። ነገር ግን የጌታችን እናቱ፤ ከፍጡራን በላይ የተባለች ንግሥት፤ ሰማይና ምድር የማይችሉትን አምላክ በማኅፀኗ የተሸከመች እመቤት፤ አጥብታ ያሳደገች፣ አዝላ የተሰደደች፣ በእግረ መስቀሉ ቆማ ያለቀሰች እናት፤ ሥጋዋ መፍረስ መበስበስን ያይ ዘንድ ወይም እንደሌላው ሰው እስከ ትንሣኤ ዘጉባኤ በመቃብር ይቆይ ዘንድ አይገባምና ተነሣች።

የእመቤታችን ትንሣኤ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውሃ ፈሳሽ የተደረገ ሳይሆን በቅዱስ መጻሕፍት በትንቢት የተገለጸ ነበር። ቅዱስ ዳዊት “ተንሥእ እግዚኦ ውስተ እረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ።” “አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦትም።” ይላል /መዝ. ፻፴፩፥፰/። ነቢዩ ይህንን ቃል የተናገረው ፈጣሪዬ ሆይ ምእመናንን ወደምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰምያት የመቅደስህ ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነስ ሲል ነው። ታቦት የጽላት ማደሪያ እንደሆነ ሁሉ እመቤታችንም ለክርስቶስ ማደሪያ በመሆኗ ታቦት ትባላለች።

ሌላው በመግቢያችን የገለጽነው የጠቢቡ ሰሎሞን ቃል ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ቤዛነቱን ከፈጸመ በኋላ ወደቀደመ ክብሩ እንደተመለሰ ሁሉ እመቤታችንም የክርስትናን ፍሬ ማፍራት ከአየች በኋላ በቀኙ ትቀመጥ ዘንድ “ተነሽ ነይ” ብሏቷል። ዳዊትም “በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” እንዳለ። /መዝ. ፵፬፥፱፣ ኢሳ. ፷፥፩/።

የእመቤታችን ትንሣኤ ምንም እንኳ በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ የተደረገ ቢሆንም መቃብር ክፈቱልኝ፣ መግነዝ ፍቱልኝ፣ ድንጋይ ፈንቅሉልኝ ያልተባለበትና በሦስተኛው ቀን የተፈጸመ በመሆኑ ከጌታ ትንሣኤ ጋር ይነፃፀራል።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን የቅዱሳንን ታሪክ እንናገራለን። ያቺ ዋጋው የላቀ ሽቱ በራሱ ላይ ያፈሰሰች ሴት /ማርያም ባለሽቱዋ/ ደቀመዛሙርቱ በተቃወሙ ጊዜ ከገሰጻቸው በኋላ “እውነት እላችኋለሁ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ሥፍራ በሚሰበክበት እርሷ ያደረገችው ደግሞ ለእርሷ መታሰቢያ እንደሆነ ይነገራል።” እንዳለ /ማቴ. ፳፮፥፲፫/ የቅዱሳንን ሥራ ያከበረ ጌታ የእናቱንማ እንዴት? እመቤታችንም ብእሲተ ዘካርያስ ኤልሳቤጥን በጎበኘች ጊዜ “እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል።” በማለት እንደተናገረች /ሉቃ. ፩፥፵፰/ ልደቷን፣ እድገቷን፣ መጽነስ መውለዷን፣ እረፍቷን፣ መነሳቷን መዘከር፣ መመስከር በረከትን እንደሚያስገኝ ልብ ይሏል።

የእመቤታችንን የመጀመሪያ ትንሣኤ ያየው “ትንሣኤ ሙታን የለም” ከሚሉት ከሰዱቃውያን ወገን የተጠራው ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ ነበር። ቶማስ ሀገረ ስብከቱ ሕንድ ነው። በዚያ ሲያስተምር ሰንብቶ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችንን ስታርግ ያገኛታል። ትንሣኤዋን ከእርሱ ሰውራ ያደረገች መስሎት አዘነ። “ፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” እንዲል ነገረ ማርያም፤ ከደመናው ተወርውሮ ሊወድቅ አሰበ። እርሷ ግን እርገቷን ያየ እርሱ ብቻ እንደሆነና ለሌሎችም እንዲነግራአቸው ለምልክትም እንዲሆን ሰበኗን /መግነዟን/ ሰጠችው። እርሱም ሐዋርያትን “የእመቤታችን ነገርስ እንደምን ሆነ?” ቢላቸው “አግኝተን ቀበርናት” አሉት። ቶማስም “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይሆናል?” አላቸው። ሊያሳዩትም ፈልገው መቃብሯን ቢከፍቱ ባዶ ሆኖ አገኙት። እርሱ ግን “አታምኑኝም ብዬ እንጂ እርሷስ ተንሥታ አርጋለች” በማለት ሰበኗን አሳያቸው። ለበረከትም ይሆን ዘንድ ተከፋፍለው ወደየሀገረ ስብከታቸው ሔዱ። ዛሬ በቅዳሴ ጊዜ ሠራኢው ዲያቆን በሚይዘው የመጾር መስቀል ላይ በሁለት ጆሮዎች /ቀዳዳዎች/ አልፎ በእንጨት ላይ ተጠምጥሞ የምናየው መቀነት መሰል ጨርቅ የዚያ ሰበን ምሳሌ ነው።

አንዲት ቅድስት ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያናችን በቀኖናዋ ወስና ከነሐሴ ፩-፲፭ ያሉትን ቀናት በአዋጅ የምትጾምበት ምክንያትም እንደሚከተለው ነው። እመቤታችን በአረፈች ጊዜ ሐዋርያት ቅዱስ ሥጋዋን ያሳርፉ ዘንድ ወደ ጌቴሴማኒ የመቃብር ቦታ ሲወስዷት ልማደኞች አይሁድ ተነሱባቸው “ቀድሞ ልጇን ሞተ፣ ተነሣ፣ አረገ እያሉ ሲያሳድሙ ኖሩ። ዛሬ እሷንም እንዲሁ ሊያደርጉ አይደለምን” በማለት ያቃጥሏት ዘንድ ተማከሩ። ታውፋንያ የተባለ የጎበዝ አለቃ ቀድሞ ደርሶ የአልጋውን ሸንኮር በመያዝ ከመሬት ሊጥላት ሲሞክር መልአከ እግዚአብሔር ደርሶ ሁለት እጆቹን በሰይፍ ቆርጦ ሥጋዋን ከዮሐንስ ጋር ወደ ገነት አሳረገ። በዚያም በዕፀ ሕይወት ዛፍ ሥር አስቀምጧት ጻድቃን ሰማዕታት ሲዘምሩላት፣ እነዳዊት በበገና፣ እነዕዝራ በመሰንቆ ሲያመሰግኗት ቆዩ። ሐዋርያትም ሥጋዋን አግኝተው ይቀብሯት ዘንድ ከነሐሴ ፩ ጀምሮ እስከ ፲፬ ሁለት ሱባኤ ያዙ። በ፲፬ኛው ቀን ጌታ ሥጋዋን ሰጥቷቸው በፍጹም ደስታ በጌቴሴማኒ አሳረፏት። በሦስተኛውም ቀን ተነሥታ ስታርግ ቶማስ ተመለከታት።

እንግዲህ የእመቤታችንን ትንሣኤ ከቶማስ በቀር ሌሎች አላዩም ነበርና በዓመቱ ከያሉበት ተሰባስበው ጾም ጸሎት ጀመሩ። የለመኑትን የማይነሳ፣ የነገሩትን የማይረሳ አምላካችንም መላውን ሐዋርያት ወደ ገነት አውጥቶ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረው መቃብር እመቤታችንን ነፍስዋን ከሥጋዋ አዋሕዶ አንሥቶ፣ ትንሣኤዋንና እርገቷን አሳይቶ፣ ለዓለም ይህንን እንዲያስተምሩ አዘዛቸው። ከዚያን ጊዜ በኋላ የተነሱ አበውና እኛም በሥጋ ዓይናችንም ባይሆን በመንፈሳዊ ዓይናችን ትንሣኤዋን እናይ ዘንድ፣ በረከቷን ረድኤቷን አሳድራብን ከልጇ ከወዳጇ ምሕረትን ይቅርታን ትለምንልን ዘንድ፣ ጾመን ጸልየን ትንሣኤዋን በፍጹም ደስታ እናከብራለን።

ጾም ጥሬ ቃሉ መከልከል፣ ለተወሰነ ጊዜ ከምግብ፣ ከመጠጥ ወዘተ መታቀብ ማለት ነው። ጾም ደማዊት ነፍስን ለነባቢት ነፍስ የምታስገዛ ደገኛ ሥርዓት ነች። አዳም ከአምላኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠው ትእዛዝ “አትብላ” የሚል ነበር። ይህም የፈጣሪነትና የፍጡርነት መለያ፣ ጾምንም ማስተማሪያ ነው። ይህ ትእዛዝ በመጣሱም ሞት ወደ ዓለም ገብቷል። ጾም ወደ እግዚአብሔር ያቀርባል። /ኢዩ. ፩፥፲፬፣ ፪፥፲፪/። ጾም እግዚአብሔርን ለመለመንና በረከትን ለመቀበል ያስችላል። /ዮና. ፫፥፰-፲፣ ዳን. ፱፥፭-፰/።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ፴ ዓመቱ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ከተጠመቀ በኋላ ለማስተማር ከመውጣቱ በፊት ወደገዳመ ቆሮንቶስ በመሔድ ፵ መዓልትና ሌሊት ጾሟል። /ማቴ. ፬፥፪/። ይህንንም አብነት አድርገው ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ በመላው ዓለም ለስብከት ከመሰማራታቸው በፊት ጾመ ሐዋርያት ተብሎ የተሰየመውን ጾመዋል።

ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዮስ መልእክቱ “በቀረውስ ወንድሞች ሆይ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ በጎነት ቢሆን ምሥጋና ቢሆን እነዚህን አስቡ ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል” በማለት እንዳስተማረን /ፊል. ፬፥፱/ የአባቶቻችንን አሠረ ፍኖት በመከተል በሕገ እግዚአብሔር በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንጓዛለን።

ለጻድቃን ለሰማዕታት ለሐዋርያት ለነቢያት የተለመነች እናታችን ለእኛም ትለመነን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዋቢ መጻሕፍት፦
    ፩. መጻሕፍተ ሰሎሞን ወሲራክ
    ፪. ተአምረ ማርያም
    ፫. ወላዲተ አምላክ በኢትዮጵያ
    ፬. ወላዲተ አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ
    ፭. ውዳሴ ወቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ

Thursday, August 11, 2011

ትንሣኤ ግዕዝ


 
/ርት ፀደቀ ወርቅ አስራት

የጥንቱ ውበቱ
ጭራሽ ተዘንግቶ፣
ለብዙ ዘመናት
የሚያስታውስ አጥቶ፣
ተዳክሞ ቢያገኙት
ግዕዝ አንቀላፍቶ፣ 
«ሞተ ሞተ» ብለው
አዋጅ አስነገሩ፣
በርቀት እያዩ
ቀርበው ሳያጣሩ፡፡
ታዲያ ይሄን ጊዜ.....
አዋጁን የሰሙት
ቀርበው ወገኖቹ፣
ፍፁም እያነቡ
ግዕዝ..... ግዕዝ ቢሉ
አብዝተው ቢጣሩ፣
በቅፅበት ተነሣ፣
ትንሣኤን አግኝቶ
ለወዳጆቹ ጥሪ
ምላሽ ሊሰጥ ሽቶ፡፡