Monday, August 22, 2011

እግር ያለው ባለ ክንፍ

 ምክንያተ ጽሕፈት ይህንን ጽሑፍ በዚህ ጊዜ እንድጽፍ ምክንያት የሆነኝ ወዳጄ በዕውቀቱ ሥዩም ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ልዩ ልዩ አካላት የሚያቀርቧቸውን ሃሳቦች የሚተነትን አንድ ጥናታዊ ነገር እየሠራሁ ነበር፡፡ በመካከል ሐራሬ እያለሁ በዕውቀቱ «እግር አልባ ባለ ክንፍ» ብሎ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ አንድ ጽሑፍ አወጣ፡፡ የኛ ባህል ሃይማኖታዊ ሳይሆን ተክለ ሃይማኖታዊ ነው፤ ተክለ ሃይማኖታዊ ማለትም በሰማዩ ላይ ያለ ቅጥ በማንጋጠጥ ምድርን ማጣት፣ በዚህም ለድህነት መዳረግ ማለት ነው የሚል ነው ሃሳቡ፡፡   ይህ ጽሑፍ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ታሪክ እና ማንነት የወቅቱ መወያያ እንዲሆን አደረገው፡፡ እኔም ይህንን እንዳዘጋጅ ምክንያት ሆነኝ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ሌሎች አካላት የሚያነሷቸውን ሃሳቦችም ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ የበዕውቀቱን ሃብ ደግሞ ለብቻው፡፡  አቡነ ተክለ ሃይማኖት ማናቸው? አቡነ ተክለ ሃይማኖት በ1186 ዓም በሰሜን ሸዋ ቡልጋ ጽላልሽ ተወለዱ፡፡ አባታቸው የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሲያስተምሯቸው አካባበቢያቸው ደግሞ በዘመኑ የነበሩ ልጆች ይማሩ የነበረውን ፈረስ መጋለብን፣ ቀስት መወርወርን፣ እርሻን እና አደንን አስተምረዋቸዋል፡፡ በሰባት ዓመታቸው ከግብፃዊው አቡነ ቄርሎስ ዲቁናን ከተቀበሉ በኋላ እግዚአብሔር በክህነት ሕዝቡን እንዲያገለግሉ መረጣቸው፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ለክህነት መጠራት በዚህ ዓለም ትዳር መሥርቶ፣ የዓለሙንም ሥራ ሠርቶ መኖር አያስፈልግም ከሚል ፍልስፍና የመነጨ አይደለም፡፡ ከ8ኛው መክዘ ጀምሮ በሀገሪቱ የመንፈስ መቀዛቀዝ ይስተዋል ነበር፡፡ ዮዲት ጉዲት መንግሥቱን ይዛ በክርስትናው ላይ ከዘመተች በኋላ ሰሜኑ እና ደቡቡ ተቆራርጧል፡፡ የሃሳብን ልዕልና የሚያመጣው የመንፈስ ልዕልና ተዳክሟል፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያን የሚዋጅ ኢትዮጵያዊ ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህ ነው የተክለ ሃይማኖት የጥሪ ምክንያት፡፡  አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከአባታቸው ዕረፍት በኋላ ቅስናን ከአቡነ ቄርሎስ ተቀብለው በጽላልሽ አካባቢ በክህነት ከአባታቸው ጋር አገልግለዋል፡፡ አባታቸው ሲያርፉ በወንጌሉ ማንም ሊከተለኝ የሚወድድ ቢኖር  ያለውን ሁሉ ትቶ መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ ያለውን በመከተል ሀብታቸውን ለድኾች መጽውተው ለወንጌል ስብከት ወጡ፡፡ የዋልድባው ገድለ ተክለ ሃይማኖት ወደ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ ከመሄዳቸው በፊት ቅስናን ተቀብለው በሸዋ እና በዳሞት ማገልገላቸውን ይገልጣል፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዳሞት እና በሸዋ ካገለገሉ በኋላ መጀመርያ ደቡብ ወሎ ቦረና ወደ ነበረው ወደ ደብረ ጎል ገዳም ገብተው አሥር ዓመት(12 የሚልም አለ) በትምህርት እና በሥራ አሳልፈዋል፡፡ በዚያም ዋሻ ፈልፍለው አስደናቂ ሕንፃ ሠርተው ነበር፡፡ ገድለ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ እንደሚለው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ ሐይቅ የገቡት በሠላሳ ዓመታቸው ነው፡፡ ይህም የሚያሳየን በሸዋ እና በወላይታ ያገለገሉት ገና በወጣትነታቸው ጊዜ መሆኑን ነው፡፡ በ1216 ዓም አካባቢ ወደ ሐይቅ የገቡት አቡነ ተክለ ሃይማኖት በሐይቅ ከመመንኮሳቸው በፊት ሰባት ዓመት ከመነኮሱም በኋላ ሦስት ዓመት በትም ህርት ፣ በሥራ እና በአገልግሎት ቆይተዋል፡፡ ሐይቅ እስጢፋኖስ በዚያ ዘመን እንደ አዳሪ ትምህርት ቤት ያለ ዩኒቨርሲቲ ነበረ፡፡ ወደዚያ የሚገባ ሁሉ ሦስት ነገሮችን ይማራል፡፡ ትምህርት፣ የጥበበ እድ ሥራ እና ሥርዓተ ምንኩስና፡፡ ትምህርቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን መላ ትምሀርት ያካትታል፡፡ የሞያ ትምህርቱም መጻፍ፣ መደጎስ፣ ሕንፃ ማነጽ፣ ልብስ መሥራት፣ እርሻ፣ የከብት ርባታ እና የሥዕል ሥራን ይመለከታል፡፡ ከእነዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ጽሙድ እንደ ገበሬ ቅኑት እንደ በሬ እንዲሆኑ ሥርዓተ ምንኩስናን ይማራሉ፡፡ በእነዚህ ትምህርቶች የታነፁት መነኮሳት ከገዳሙ ሲወጡ ዛሬ የፒኤች ዲ ተማሪ ዴዘርቴሽን እንደሚያቀርበው የተማ ሩትን ጽፈው አንድ የብራና መጽሐፍ አዘጋጅተው ይወጣሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ሐይቅ ከስምንት መቶ መነኮሳት በላይ በአንድ ጊዜ የሚማሩባት በመጻሕፍትም የበለጸገች ዩኒቨርሲቲ ነበረች፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እዚህ ነው አሥር ዓመታትን ያሳለፉት፡፡ ከሐይቅ ወጥተው በዘመኑ በሥርዓተ ምንኩስና እና በትምህርት ብሎም በጥበበ እድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ወደ ነበረው ወደ ደብረ ዳሞ ሄዱ፡፡ በዚያም ከአቡነ ዮሐኒ ዘንድ መንፈሳዊ ትምህርት፣ ሥርዓተ ምንኩስና እና ጥበበ እድ ሲማሩ ሰባት ዓመት አሳለፉ፡፡ ያነጹት ፍልፍል ድንጋይ ዋሻ፣ መጻሕፍት ሲጽፉ ቀለማቸውን ያስቀምጡባቸው የነበሩትን ሽንቁሮች ዛሬም በደብረ ዳሞ ማየት ይቻላል፡፡ ቀሪዎቹን አምስት ዓመታት ሌሎችን የትግራይ ገዳማት እየተዘዋወሩ ሲመለከቱ ቆይተው ከሸዋ በወጡ በሃያ ሁለት ዓመት እድሜያቸው ሃምሳ ሁለት ሲሆን ለበለጠው ክብር እና ርእይ በግብጽ በኩል ወደ ኢየሩሳሌም ተሻገሩ፡፡ ከኢየሩሳሌም ሲመለሱ በሐይቅ በኩል አድርገው ደብረ ጎልን ተሳልመው በሚዳ እና በመርሐ ቤቴ በኩል ወደ ሸዋ በመምጣት ከዮዲት ዘመን በኋላ በመንፈሳዊ ሕይወት የተጎዳውን ሸዋን እና ደቡብ ኢትዮጵያን በመዘዋወር ለአሥር ዓመታት ያህል አስተምረዋል፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተግተው በማስተማራቸው የተኛው ሁሉ ነቃ፣ የደከመው በረታ፣ የጠፋውም ተገኘ፡፡ በስብከታቸው እንደገና ለነቃው ለመካከለኛው እና ለደቡብ ኢትዮጵያ ሐዋርያትን ለማፍራት እንዲችሉ አንድ ገዳም ለመመሥረትና ደቀ መዛሙርትን ለማስተማር አሰቡ፡፡ እናም ወደ ደብረ አስቦ ገዳም ገቡ፡፡ ቦታውን አስተካክለው እና ከደብረ ዳሞ እና ከሐይቅ የተከተሏቸውን ጥቂት ደቀ መዛሙርት ይዘው በደብረ ሊባኖስ ገዳም ልክ እንደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ሁሉ ሦስቱን ነገሮች ያካተተ አገልግሎት ጀመሩ፡፡ ምንኩስና፣ ትምህርት እና ሥራ፡፡ መነኮሳቱ መንፈሳዊ ትምህርት ይማራሉ፤ በሕገ ገዳም ይመራሉ፤ ለራሳቸው እና ለአካባቢው ሕዝብ ርዳታ የሚሆን እርሻ ያርሳሉ፡፡ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው፣ ገዳማቸውን አደራጅተው፣ ስብከተ ወንጌልንም አስፍተው አስፍተው ሰያደ ላድሉ በሕይወታቸው የመጨረሻ ዓመታት ወደ ደብረ አስቦ ዋሻ ገብተው በአንድ እግራቸው በጾም እና በጸሎት ተወሰኑ፡፡ በጸሎት ብዛትም እግራቸውን በማጣታቸው ስለ ክብራቸው ከእግዚአብሔር ክንፍ ተሰጥቷቸዋል፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አገልግሎታቸውን ፈጽመው ነሐሴ ሃያ አራት ቀን 1287 ዓም በ99 ዓመታቸው ዐረፉ፡፡  ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚነሡ ጥያቄዎች አቡነ ተክለ ሃይማኖት እና የመንግሥት ለውጥ አንዳንዶች «ከዛግዌ ሥርወ መንግሥት ወደ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት የተደረገውን ሽግግር ያከናወኑት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ናቸው፡፡ ይህንንም ያደረጉት ይኩኖ አምላክ የሸዋ ሰው ስለሆነ ለዘራቸው አድልተው ነው» ይላሉ፡፡ በሸዋው ይኩኖ አምላክ እና በዛግዌ ሥርወ መንግሥት ወራሹ በነአኩቶ ለአብ መካከል መቀናቀን የተጀመረው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሐይቅ በትምህርት ላይ በነበሩበት ጊዜ ነበር፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕፃን በነበሩበት ጊዜ ከዳሞት የሚመጣው የሞተለሚያውያን ኃይል ሸዋን ደጋግሞ በመውረር አብያተ ክርስቲያናትን ዘርፏል ሕዝቡንም ማርኳል፡፡ ይህ ጉዳይ የሸዋን ሕዝብ ማስቆጨቱ እና ማነሣሣቱ የማይቀር ነው፡፡ በተለይም ከአኩስም የተሰደደው የሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት ዘር ሸዋ መንዝ ነው የገባው ተብሎ በሚታመንበት ሁኔታ ሸዋዎች ራሳቸውን ለመከላከል መደራጀት ጀምረዋል፡፡ ደቡቡ ኢትዮጵያ ከማዕከላዊው መንግሥት መቀመጫ ከሮሐ እየራቀ ሄዶ ስለነበር ለይኩኖ አምላክ ጥሩ መደላድል ሆኖታል፡፡ ገድለ ኢየሱስ ሞዓ እንደሚተርከው የመንግሥትን ነገር ከይኩኖ አምላክ ጋር የተነጋገሩት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሳይሆኑ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ ናቸው፡፡ ያን ጊዜ ደግሞ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በተማሪነት ሐይቅ ገዳም ውስጥ ነበሩ፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ እና ይኩኖ አምላክ በመንግሥት ጉዳይ ላይ ለመነጋገር የበቁት ይኩኖ አምላክ በሸዋ ላይ ይደርስ ከነበረው የሞተለሚ ጥቃት ሸሽቶ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርት ቤት ወጣትነቱን ያሳለፈ በመሆኑ ነበር፡፡ ሁለቱ ባደረጉት ስምምነት የዐቃቤ ሰዓትነትን መዓርግ ለሐይቅ ገዳም መምህር እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህም ማለት የንጉሡ ገሐዳዊ ግንኙነቶች በዐቃቤ ሰዓቱ በኩል እንዲፈጸሙ ማለት ነው፡፡      የንጉሡ ደብዳቤ ወደ ሐይቅ ገዳም ሲላክ መነኮሳቱ ተቀምጠው እንዲሰሙ     ለገዳሙ የተሰጠውን መሬት የመኳንንቱም ሆነ የነገሥታት ልጆች እንዳይነኩ     ነፍስ የገደለ፣ ንብረት የሰረቀ፣ እግረ ሙቁን ሰብሮ እዚህ ገዳም ገብቶ ቢደውል ከሞት ፍርድ እንዲድን     ለገዳሙ የተሰጠው ርስት ለአገልጋዮች ብቻ ስለሆነ ዘር ቆጥሮ ማንም ተወላጅ እንዳይወርስ     የገዳሙ ርስት መነኩሴ ላልሆነ ጥቁር ርስት እንዳይሰጥ  የሚሉት ታወጁ፡፡ ይህ ሁሉ ሲከናወን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሐይቅ ትምህርት ላይ ነበሩ፡፡ በኋላ ዘመን ይኩኖ አምላክ ኃይሉ እየበረታ ነአኩቶ ለአብም ግዛቱ እየጠበበ እና ኃይሉ እየደከመ ሲሄድ ከወሎ በታች ያለውን ሀገር የያዘው ይኩኖ አምላክ እና ላስታን እና ሰሜኑን የያዘው ይኩኖ አምላክ ለጦር ይፈላለጉ ጀመር፡፡ በዚህ ዘመን ነበር አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከኢየሩሳሌም የተመለሱት፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ያደረጉት ነገር ቢኖር ኃይሉ እየገነነ የመጣውን ይኩኖ አምላክን እና የወቅቱን ንጉሥ ነአኩቶ ለአብን ማደራደር ነበር፡፡ ይኩኖ አምላክ ለመንገሥ ከቅብዐት በቀር የቀረው ኃይል አልነበረም፡፡ የነአኩቶ ለአብ ኃይል ደግሞ ቢዳከምም አልሞተም፡፡ ሁኔታው ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳይሄድ ያሰጋቸው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሁለቱን በማደራደር ከአንድ ስምምነት ላይ አደረሷቸው፡፡      ይኩኖ አምላክ ምንም ኃይል ቢኖረው ነአኩቶ ለአብ እስኪያርፍ ድረስ ንግሥናውን እንዳያውጅ     ከነአኩቶ ለአብም በኋላ የዛግዌ ዘር የላስታን አውራጃ እንዲገዛ     የላስታው ገዥ በፕሮቶኮል ከንጉሡ ቀጥሎ እንዲሆን  ይህ ስምምነት ባይኖር ኖሮ ጦር በሰበሰበው በይኩኖ አምላክ እና ሥልጣን ላይ በነበረው በነአኩቶ ለአብ መካከል በሚፈጠረው ጦርነት የሀገሪቱ ልጆች ባለቁ ነበር፡፡ ዛሬ ቢሆን ይሄ ተግባር የኖቬል ሽልማት የሚያሸልም ነበር፡፡ ይህ ስምምነት በኋላ በዐፄ ይትባረክ ዘመን በመፍረስ የተከሰተውን ጦርነት ያየ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ያደንቃል እንጂ አይተችም፡፡ ሲሦ መንግሥት አንዳንዶች «አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት በዋሉት ውለታ ለቤተ ክርስቲያን ሲሦ መንግሥት ተሰጠ» ይላሉ ይኩኖ አምላክ ሲነግሥ በኢትዮጵያ ውስጥ ጳጳስ አልነበረም፡፡ ከአቡነ ጌርሎስ ሞት በኋላ ከግብፅ የመጣ ጳጳስ አልነበረም፡፡ ይህ ሁኔታ በመንፈሳዊ ትንሣኤ ላይ ለነበረችው ኢትዮጵያ የአገልጋዮች እጥረት አስከተለ፡፡ በዚህ ጊዜ የተሰባሰቡት የኢትዮጵያ ሊቃውንት በትምህርትም በአገልግሎትም የበረቱትን አቡነ ተክለ ሃይማኖትን መረጡ፡፡ የሚሾም ሲኖዶስ አልነበረምና እግዚአብሔር «ሐዋርያትን በሾምኩበት ሥልጣን ሾምኩህ» አላቸው፡፡ ይኩኖ አምላክ ምንም እንኳን በንግሥናው ቢገዛ እንደ ወጉ ሥርዓተ መንግሥት አልተፈጸመለትም ነበር፡፡ በመሆኑም በዘመኑ የነበሩት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥርዓተ መንግሥቱን ፈጸሙለት፡፡ እርሱም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ርስት ሰጠ፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ርስት መስጠት በይኩኖ አምላክ የተጀመረ አይደለም፡፡ እንዲያውም ቅዱስ ላሊበላ ለአኩስም፣ ለላሊበላ፣ ለመርጡለ ማርያም እና ለተድባበ ማርያም የሰጠው ርስት ይበልጣል፡፡ በወቅቱ ለሐዋርያዊ አገልግሎት እና ለተማሪዎች ድርጎ ለቤተ ክርስቲያን ጥሪት ያስፈልጋት ስለነበር ይኩኖ አምላክ ርስት ሰጥቷል፡፡ ይህ ግን ከመንግሥት ዝውውር ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ዛሬም ቢሆን እኮ አንዳንድ የአውሮፓ ሀገሮች ለቤተ ክርስቲያን የተለየ በጀት ይሰጣሉ፡፡ እጨጌ የሚለውን ስም ከርስት አስተዳዳሪነት ጋር የሚያገናኙት ሰዎች አሉ፡፡ እጨጌ የሚለውን ስም ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት የሰጣቸው መንግሥት ሳይሆን የወላይታ ሕዝብ ነው፡፡ በወላይተኛ «ጨጌ» ማለት «ሽማግሌ፣ ታላቅ፣ አባት» ማለት ነው፡፡ ወደ አማርኛ ሲመጣ «እጨጌ» ተባለ፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን አገልግሎት አይቶ ይህንን የሰጣቸው ሕዝቡ ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥልጣን ወዳድ አለመሆናቸውን በግልጽ አሳይተዋል፡፡ ከብዙ ዘመናት በኋላ አቡነ ዮሐንስ 5ኛ ከግብጽ መጥተው አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በግማሽ ኢትዮጵያ በመንበረ ጵጵስና እንዲያገለግሉ ለምነዋቸው ነበር፡፡ እርሳቸው ግን ለሥልጣን ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጸው እንዲያ ሕዝብ ሲወዳቸው እና ሲፈልጋቸው ወደ በኣታቸው ነው የተመለሱት፡፡ «ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሌላ ናቸው »    አንዳንዶች «በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከ8 እስከ 13ኛው መክዘ ባለው ጊዜ የኖሩ ሌላ ተክለ ሃይማኖት የሚባሉ ጻድቅ ነበሩ፡፡ የርሳቸው ታሪክ ከሌላ ተክለ ሃይማኖት ታሪክ ጋር ተዳብሎ አሁን ያለWን ገድለ ተክለ ሃይማኖት አስገኘ፡፡ እናም ጻድቁ ተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ አይደሉም » ይላሉ  እስካሁን ድረስ ይህንን አባባል የሚጠቅሱ ሰዎች ያቀረቡት ማስረጃ የላቸውም፡፡ እገሌ አይቶት ነበር፡፡ እዚህ ገዳም ነበር ከማለት ውጭ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ለሌለ ማስረጃ ሲባል ያለ ማስረጃ አይሰረዝም፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስን በተመለከተ ያሉት ማስረጃዎች አራት ዓይነት ናቸው፡፡      ገድላቸው     የሌሎች ቅዱሳን ገድሎች     ዜና መዋዕሎች እና     የግብፅ ቤተ ክርስቲያን መረጃዎች  ገድለ ተክለ ሃይማኖት እኔ ለማየት የቻልኩት የደብረ ሊባኖስ፣ የሐይቅ እስጢፋኖስ፣ የዋልድባ፣ የጉንዳንዳጉንዲ እንዲሁም ዐፄ ምኒሊክ ወላይታን ሲወጉ ያገኙት የወላይታ ገድለ ተክለ ሃይማኖት ቅጂዎች አልፎ አልፎ ከሚያሳዩት መለያየት በስተቀር የሚተርኩት በ13ኛው መክዘ ስለነበሩት ተክለ ሃይማኖት ነው፡፡ እኒህ ተክለ ሃይማኖት ጽላልሽ ተወልደው፣ በኢትዮጵያ ገዳማት ተምረው፣ በመላ ሀገሪቱ ሰብከው፣ ግብጽ እና ኢየሩሳሌም ተሻግረው፣ ደብረ ሊባኖስን መሥርተው ያገለገሉትን ተክለ ሃይማኖት ነው የሚናገሩት፡፡ ሌላው ቀርቶ ወሎ ጉባ ላፍቶ፣ ጎንደር አዞዞ ተክለ ሃይማኖት የተገኙት ገድላትም ተመሳሳይ ታሪክ ነው የሚተርኩት፡፡ እስካሁን ከኒህኛው ተክለ ሃይማኖት ውጭ ስላሉ ሌላ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚተርክ ገድል አልተገኘም፡፡ አለ ከመባል በቀር፡፡ የኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍትም ሆኑ በአካል ያልተገኙት ማይክሮ ፊልሞቻቸው በተከማቹባቸው በብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ወመዛግብት፣ በመንበረ ፓትርያርክ ሙዝየም እና ቤተ መጻሕፍት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ቤተ መጻሕፍት፣ በብሪቲሽ ሙዝየም እና ቤተ መጻሕፍት፣ በቫቲካን ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት፣ አሜሪካ ኮሌጅቪል በሚገኘው ቅዱስ ዮሐንስ ኮሌጅ ያሉትን ማይክሮ ፊልሞች እና የብራና መጻሕፍት ዝርዝሮችን ብናይ ስለ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ እንጂ ስለ ሌላ ተክለ ሃይማኖት የተጻፈ ገድል የለም፡፡ (የዚህን ዝርዝር የጥናት ውጤት በቅርብ ለኅትመት አበቃዋለሁ፡፡) ሌሎች ገድሎች  ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚያነሡ አያሌ ገድሎች አሉ፡፡ ገድለ አኖሬዎስ ዘሞረት፣ ገድለ አቡነ አኖሬዎስ ዘወረብ፣ ገድለ አቡነ ፊልጶስ፣ ገድለ አቡነ ኤልሳዕ፣ ገድለ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ፣ ገድለ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ፣ ገድለ አቡነ ቀውስጦስ፣ ገድለ አቡነ ማትያስ፣ ገድለ አቡነ ታዴዎስ ዘጽላልሽ፣ ገድለ አቡነ ገብረ ክርስቶስ ዘግድም፣ ገድለ አቡነ መርቆሬዎስ ዘመርሐ ቤቴ፣ ገድለ አቡነ አድኃኒ ዘዳሞት፣ ገድለ አቡነ ኢዮስያስ ዘወጅ፣ ገድለ አቡነ ዮሴፍ ዘእናርያ፣ ገድለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እና ሌሎች ወደ አሥራ ሦስት የሚጠጉ ገድላት ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተጨማሪ መረጃዎች ይሰጣሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ገድላት የሚያነሷቸው ተክለ ሃይማኖት ግን ተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስን ነው፡፡ ዜና መዋዕሎች የይኩኖ አምላክ፣ የዓምደ ጽዮን፣ የዘርዐ ያዕቆብ፣ የሱስንዮስ፣ እና የሌሎቹም ዜና መዋዕሎች ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ ይተርካሉ፡፡ ግብፃውያን መዛግብት የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ቅዱሳን መካከል አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንዱ ናቸው፡፡ እንዲያውም ቤተ ክርስቲያንዋ የአራት ቅዱሳንን ብቻ የልደት በዓል ታከብራለች፡፡ የጌታን፣ የእመቤታችንን፣ የዮሐንስ መጥምቅን እና የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን፡፡ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጥንታውያንም ይሁኑ ዘመናውያን መዛግብት የሚገልጹት በ12ኛው መክዘ ጽላልሽ ተወልደው ስላደጉት ስለ ደብረ ሊባኖሱ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ነው፡፡ እናም ወደፊት አዲስ ነገር ተገኘ ስንባል ያን ጊዜ እንከራከር ካልሆነ በቀር እስካሁን ድረስ ግን ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር የታሪክ ዝምድና ያላቸው ሌላ ተክለ ሃይማኖት መኖራቸውን የሚገልጥ ማስረጃ የለም፡፡ «አቡነ ተክለ ሃይማኖታዊ» ትውልድ በዕውቀቱ ሥዩም ምድርን ትቶ ሰማይ ሰማይን ብቻ ሲመኝ በድህነት የሚዳክር ትውልድን «ተክለ ሃይማኖታዊ» ብሎ ሰይሞታል፡፡ ይህ የበዕውቀቱ ሥያሜ ከሁለት ነገሮች የመጣ ይመስለኛል፡፡ አንደኛው ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ካለ የግንዛቤ ማነስ እና ሁለተኛው ከታሪክ ተፋልሶ የተነሣ፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በሦስት ሥርዓተ ትምህርቶች በተቃኘው የሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርት ቤት የኖሩ ናቸው፡፡ በትምህርት፣ በሥራ እና በምንኩስና፡፡ ሥራ ለዓለማውያን ብቻ ሳይሆን ለመነኮሳትም የግድ አስፈላጊ መሆኑን የተማሩም ያስተማሩም ናቸው፡፡ በተጓዙባቸው ቦታዎች ሁሉ ሦስቱንም ሲያከናውኑ ነው የኖሩት፡፡ በመጨረሻም ወደ ደብረ አስቦ ሲገቡ ገዳማዊው ሥርዓታቸው ትምህርትን፣ ምንኩስናን እና ሥራን ያዋሐደ ነበር፡፡ እናም «ተክለ ሃይማኖታዊ» ማለት «እየሠራ የሚጸልይ፣ እጸለየ የሚሠራ» ማለት እንጂ በሰማዩ ላይ ብቻ ያለ ቅጥ እያንጋጠጡ ምድራዊ ሕይወትን መዘንጋት እና ለድህነት መዳረግ ማለት አይደለም፡፡  እኔ ይህንን ስል ምድራዊ ሕይወት እንደማያስፈልግ የሚያስተምሩ፣ ሥጋ እንዳልተፈጠረ ቆጥረው በሥጋ መኖርን የሚያጣጥሉ የሉም ማለቴ አይደለም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት በሥጋ ተጋብቶ፣ ወልዶ ከብዶ፣ አርሶ ነግዶ፣ ወጥቶ ወረዶ መኖርን የሚያንቋሽሽቱ እና ለነፍስ ብቻ መኖር አለብን የሚሉት ማኔያውያን ተወግዘዋል፡፡ በዕውቀቱ ላነሣው ሃሳብ ትክክለኛ ስያሜውም «ማኔያዊ» እንጂ ተክለ ሃይማኖታዊ አይደለም፡፡ እግር እና ክንፍ በዕውቀቱ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እግራቸውን ያጡት ክንፍ ለማብቀል ሲሉ እንደሆነ አድርጎ ያስቀምጠዋል፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትኮ ክንፍ ያገኙት እግራቸውን ከማጣታቸው በፊት ነው፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ዘንድ አገልግለው ሲፈጽሙ ወደ ምድር በገመድ ወረዱ፡፡ የደብረ ዳሞ መውጫ እና መውረጃው ገመድ ነውና፡፡ ያለፈውን ትጋታቸውን፤ የወደፊቱን አገልግሎታቸውን ያየ ሰይጣን የሚወርዱበትን ገመድ በጠሰባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር አክናፈ ጸጋ ሰጥቷቸው ከተራራው ሥር ሁለት ሺ ክንድ ያህል ርቀው በሰላም ዐረፉ፡፡ ያም ቦታ በኋላ ዘመን በስማቸው ቤተ ክርስቲያን ተተክሎበታል፡፡ እናም ገና ሁለት እግር እያላቸው፤ ተዘዋውረው በሚያስተምሩበት ጊዜ፣ ግብፅ እና ኢየሩሳሌም ከመሄዳቸው በፊት ነው ክንፍ የተሰጣቸው፡፡ ታድያ ሁለት እግር እያላቸው ያገኙትን ክንፍ ለማግኘት እግር ማጣት ለምን ያስፈልጋቸዋል? አቡነ ተክለ ሃይማኖት በአንድ እግራቸው የጸለዩት በቅድመ ጲላጦስ የቆመውን ክርስቶስን በማሰብ እንጂ ክንፍ ለማግኘት ሲሉ አይደለም፡፡ እንደ ወንድሜ እንደ በዕውቀቱ አገላለጥ አቡነ ተክለ ሃይማኖት «እግር አልባ ባለ ክንፍ» ሳይሆኑ «ክንፍ ያለው ባለ እግር ናቸው» አቡነ ተክለ ሃይማኖት በእግር የሚደረስበትን የዘመኑን ቦታ ሁሉ ደርሰውበታል፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ ዙረዋል፡፡ ግብጽ ወርደዋል፤ ኢየሩሳሌም ወጥተዋል፡፡ መንግሥተ እግዚአብሔር ደግሞ በጸጋ ክንፍ እንጂ በእግር አይደረስባትምና ወደ ሰማያዊው ኢየሩሳሌም ሄደው እንዲያዩ አስቀድሞ የሰጣቸውን ክነፍ እግራ ቸው በተቆረጠ ጊዜ ገልጦላቸዋል፡፡ ያንጊዜም በእግር ወደማይደረስበት ሰማያዊ መቅደስ ገብተው ከሱራፌል ጋር አጥነዋል፡፡ በእግር የሚደረስበትን ለፈጸመ ሰው ከክንፍ ውጭ ምን ሊሰጠው ኖሯል? በእንተ በዕውቀቱ ሥዩም ሀገራዊ መንፈስ ፍለጋ በዕውቀቱ ሥዩም ነገሮችን በአዲስ መልክ ከሚያዩ ጥቂት የሀገራችን ጸሐፍት አንዱ ነው፡፡ ገና ብዙ ሥራ የሚጠበቅበት ወጣት ጸሐፊም ነው፡፡ ሕይወቱን ለጽሑፍ የቀየደ ሰውም ነው፡ እኔ በዕውቀቱ ሥዩም ይህንን ጽሑፍ ሲጽፍ ዓላማው ቤተ ክርስቲያንን መፃረር ነው ብዬ ኣላምንም፡፡ በጽሑፉ መግቢያ እንደገለጠው ነባሩን ባህል በዓለማዊ መነጽር ማየት እፈልጋለሁ ነው ያለው፡፡ ይህም ማለት የእስላሙንም የክርስቲያኑነም፣ ሃይማኖታዊውንም ሃይማኖታዊ ያልሆነውንም ነባር ባህል በ «ዓለማዊ´E መነጽር ሊያይ ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ አንድን ነገር በፈለገው መንገድ ማየት የተፈጽሮ መብቱ ነው፡፡ በዚህ አንከራከረም፡፡ በዕውቀቱ እንደዚህ ያለ ነባር፣ ሕዝብ የተቀበለውን እና መከራከርያ ያለውን ነገር ሲያይ እንደሌላው ነገር በሳቅ በሥላቅ፣ በቀልድ፣ በእግረ መንገድ ባያደርገው ግን እመርጣለሁ፡፡ ካነሣ ጠንካራ መከራከርያ አንሥቶ መሞገት ነው ያለበት፡፡ በአሁኑ ጽሑፉ ግን ይህንን አላየሁበትም፡፡ በዕውቀቱ እንደሚለው ለርሱ ዋናው ሃሳቡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ መከራከር ሳይሆን በአቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድ ነቁጥ ታሪክ እንደርሱ አገላለጥ «እግር አጥተው ክንፍ ባወጡበት» ታሪክ ተምሳሌትነት የሕዝቡን ነባር ሁኔታ ማየት ነው፡፡ ይህም ቢሆን ግን ሕዝቡ ለሌላ ነገር ሲጠቀምበት የኖረውን ስያሜ አንሥቶ ምንም ዓይነት በቂ መከራከርያ ሳያቀርብበት ለሌላ ነገር ከሚጠቀም ይልቅ ሌላ ስያሜ ቢጠቀም የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ «ተክለ ሃይማኖታዊ» የሚለው ማሳያ ከእውነታው ውጭ ቀርቧልና፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዕውቀቱን አደንቀዋለሁ፡፡ ብዙ ጸሐፊዎች ከውጭ በመጣ ሃሳብ ኢትዮጵያን ማየት ሲመርጡ በሀገራዊ ተምሳሌት እና ሃሳብ ራሳችንን ለማየት መሞከሩ በዕውቀቱ ውርጅናሌውን የያዘ ጸሐፊ ነው እንድልም አድርጎኛል፡፡ ምንም እንኳን «ተክለ ሃይማኖታዊ» ብሎ በሰጠው ሥያሜ ትርጉም ባልስማማም ሀገርኛ ስያሜ እና ተምሳሌት ለመምረጥ መጣሩን ግን አደንቃለሁ፡፡ በ1956 ዓም «የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ» የምትል ትንሽ፣ ግን እጅግ ጠቃሚ መጽሐፍ ያሳተሙት እጓለ ገብረ ዮሐንስ የኢትዮጵያን ሥልጣኔ «ያሬዳዊ ሥልጣኔ» ብለው ሰይመውት ነበር፡፡ «ከሥጋ መንፈስ ይበልጣል፣ ሥጋዊ ሕይወት ወደ መንፈሳዊ ሕይወት ተመስጦ ማደግ አለበት፣ የመጨረሻው ደረጃ መንፈሳዊ አድናቆት እና ከኃይላተ ሰማይ ጋር መተባበር ነው» በሚል ዘይቤ የተቃኘ ሥልጣኔ ነው ይላሉ፡፡ እርሳቸውና በዕውቀቱን የሚያመሳስላቸው ሁለቱም ሀገራዊ ስያሜ እና መንፈስ ፍለጋ መኳተናቸው ነው፡፡ ኦርቶዶክስነት ለእኔ ኦርቶዶክስነት ሃይማኖት ብቻ አይደለም፡፡ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሀገሪቱ ውስጥ ከነበራት የእምነት፣ የታሪክ፣ የባህል፣ የሥልጣኔ፣ የትምህርት እና የሥነ መንግሥት ድርሻ አንፃር በሀገሪቱ ሕዝቦች ውስጥ እንደ ድር እና ማግ የተያያዙ ነገሮች አሏት፡፡ እንደ እኔ ግምት ሁለት ዓይነት ኦርቶዶክሶች አሉ፡፡ የሚያምኑ ኦርቶዶክሶች እና የማያምኑ ኦርቶዶክሶች፡፡ የሚያምኑት ኦርቶዶክሶች ኦርቶዶክስን የድኅነት መንገድ አድረገው የሚቀበሏት ናቸው፡፡ ዶግማዋ፣ ሥርዓቷ፣ ትውፊቷ የሚመራቸው ናቸው፡፡ የማያምኑት ደግሞ ባህልዋ፣ ፍልስፍናዋ፣ ሥርዓተ ኑሮዋ፣ ታሪኳ፣ ሥነ ምግባርዋ እና ሀገራዊ እሴ ቷን በማወቅም ባለማወቅም የተቀበሉት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ፕሮቴስታንት፣ ካቶሊክ፣ ባህላዊ እምነት አማኝ፣ እምነት የለሽ፣ ሙስሊም፣ ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በባህላቸው፣ በአስተ ሳሰባቸው፣ በታሪካቸው፣ በመሠረታቸው፣ በሥነ ምግባር እሴታቸው፣ በይትበሃላቸው እና በሀገራዊ ስሜታቸው ግን ኦርቶዶክሶች ናቸው፡፡ በተለያየ የክርስትና ባህሎች ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን እንስሳው ሁሉ ተቀድሷል እያሉ ሲያስተምሩ ቢሰሙም አይጥ እና ጉርጥ ሲበሉ፣ ወይንም ፈረስ እና አህያ አርደው ሠርግ ሲደግሱ ግን አልታዩም፡፡ በዕውቀቱ ከሁለተኛዎቹ ኦርቶዶክሶች የሚመደብ ይመስለኛል፡፡ በተደጋጋሚ እንደ ሚለው «እኔ በራሴ ትርጉም ኦርቶዶክስ ነኝ፤ የግድ እንደ እናንተ አድርጌ ማመን ግን አይጠበቅብኝም» ይህ አባባሉ ነው ከሁለተኞቹ እንድመድበው ያደረገኝ፡፡ በተደጋጋሚ ገድላቱን እና ትርጓሜያቱን ሲያነብብ እና ሲጠቅስ አየዋለሁ፡፡ ለሀገራዊ እሴቶች ዋጋ ይሰጣል፡፡ ቋንቋው «ኦርቶዶክሳዊ» ነው፡፡ የሥነ ምግባር መመሪያዎቹም እንዲሁ፡፡ በዐሉላ ቋንቋ በዕውቀቱ «ሲቪክ ኦርቶዶክስ» ነው፡፡ በዕውቀቱን የመረጠውን ሃሳብ እንዲወክልለት «ተክለ ሃይማኖታዊ» የሚለውን ቃል እንዲጠቀም ያደረገው ፀረ ቤተ ክርስቲያን ስለሆነ ሳይሆን ሲቪክ ኦርቶዶክስነቱ አይሎበት ነው ባይ ነኝ፡፡ ምንም እንኳን የትርጉም ስሕተት ቢፈጥር፡፡ አሉታዊ ጥቅም ሃይማኖት ማኅበረሰቡ የሚቀበለውና የሕይወት ሥርዓት ሆኖ የሚቀጥል ነገር ነው፡፡ እናም በማኅበረሰቡ ውስጥ ይሰርጽና ዘወትራዊ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ በመካከል ጥያቄ የሚጠይቁ፣ የተለየ ሃሳብ የሚያቀርቡ እና የሚሞግቱ ሲመጡ ግን ሃይማኖታዊ ጉዞ ከተለምዶአዊነት ወጥቶ ንቅናቄያዊ ይሆናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍቷን በቀኖና እንድትወስን፣ ሥርዓቷን እንድትወስን፣ የሃይማኖት መግለጫዋን ወስና እንድታወጣ፣ ሕግ እና ደንብ እንድትሠራ፣ መጻሕፍትን እንድትጽፍ፣ ያደረጓት እነዚህን መሰል ተግዳሮቶች በየዘመናቱ መኖራቸው ነው፡፡ ሄሊቪዲየስ ተነሥቶ በቅድስት ድንግል ማርያም ላይ የተለየ ትምህርት ባያመጣ ኖሮ አባ ጄሮም እና አባ ኤጲፋንዮስ የጻፏቸውን መጻሕፍት ባላገኘን ነበር፡፡ ቴዎድሮስ የተባለ የጦር አዛዥ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫን ስለ ሃይማኖት ባይገዳደረው ኖሮ አስደናቂውን ርቱዐ ሃይማኖት የተሰኘ መጽሐፍ ባላገኘን ነበር፡፡ የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዜና መዋዕል እንደሚነግረንም «በንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን በሃይማኖት ምክንያት ክርክር ሆነ፡፡ አባ ጊዮርጊስም ከአንድ ፈረንጅ ጋር ተከራክሮ ረታው፡፡ መጽሐፈ ምሥጢርንም ደረሰ» መልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬ ያንን የመሰለ ኮኩሐ ሃይማኖት የተሰኘ መጽሐፍ እንዲጽፉ ምክንያት የሆናቸው አባ አየለ ተክለ ሃይማኖት የሚባል ካቶሊካዊ ስለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የጻፈው ጽሑፍ ነው፡፡ እርሳቸው ባረፉ ጊዜ ይኼው ሰው እያለቀሰ መጣ አሉ፡፡ ዘመዶቻቸው ተናድደው «ደግሞ እንዴት ታለቅሳለህ?» ብለው ቢጠይቁት «እንኳንም ጻፍኩ፤ እኔ ባልጽፍ እኒህን የመሰሉ ሊቅ ገንዛችሁ ልትቀብሯቸው ነበርኮ፡፡ እኔ በመጻፌ እርሳቸውም ጻፉ፤ ምነዉ ደጋግሜ በጻፍኲ ኖሮ» አለ ይባላል፡፡ እነ አስረስ የኔ ሰው ያንን የመሰለ «ትቤ አኩስም መኑ አንተ» የተሰኘ የታሪክ፣ የእምነት፣ የቅርስ እና የሥነ ልሳን መጽሐፍ የጻፉት በወቅቱ ለተነሡት የታሪክ፣ የቋንቋ እና የእምነት ተግዳሮቶች መልስ ለመስጠት ነው፡፡ እናም የበዕውቀቱ ጽሑፍ በዚህ ረገድ ከታየ ያለንን ይበልጥ ለመግለጥ እና ይበልጥ ለማብራራት ዕድል የሚከፍት አሉታዊ ጠቀሜታ አለው ብዬም አስባለሁ፡፡ እንደነ መንግሥተ አብ ያሉ ጸሐፍትም ከእምነት ነጻነት እና ከሃሳብ ነጻነት የቱ ይበልጣል? የሚል መከራከርያ ይዘው እንዲነሡም አድርጓል፡፡ የበዕውቀቱ ጽሑፍ እና የመጻፍ ነጻነት በምንም መንገድ ይሁን በምንም እንደ በዕውቀቱ ያሉ ጸሐፍት የመጻፍ ነጻነታቸው መከበር አለበት፡፡ ጥያቄ ያለው ወይንም በሃሳባቸው የማይስማማ ሰው እስከ ሕግ አግባብ ድረስ በመሄድ ጤናማውን እና የሠለጠነውን መንገድ ተከትሎ ይሞግታል፡፡  አንድ ጸሐፊ በመጻፉ ምክንያት ብቻ አካላዊም፣ ሃሳባዊም ጥቃት እንዳይደርስበት የምንከላከለው በሚጽፈው ሃሳብ ስለምንስማማ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ለማንስማማበትም ሃሳብ ነጻነት መሟገት አለብን፡፡ ሃሳቡን እየተከራከርነውም፤ መብታችን ተደፍሯል ብለን በፍርድ ቤት እየከሰስነውም ቢሆን ለሃሳብ ነጻነቱ ግን መሟገት ግድ ይለናል፡፡  በርግጥ ልጁ ይህንን ተግባር እንደ ዓላማ የያዘ ልጅ አለመሆኑን ከጓደኞቹም ከራሱም አረጋግጫለሁ፡፡ በዕውቀቱን ይቅርታ ጠይቋል፡፡ በዕውቀቱም ይቅር ብሏል፡፡ በሃሳቡ ባይስማማም ባደረገው ነገር ግን መፀፀቱን ገልጧል፡፡ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ሚዲያዎች ሁኔታውን ያራገቡበት መንገድ ግን ነገሩ አሁንም የቀጠለ እና ሌላ አደጋ ያለ በሚያስመስል መልኩ ነው፡፡  እናም በዕወቀቱ ይጻፍ፣ የማልስማማበትንም ነገር ይጻፍ፣ እኔም የምስማማበትን እይዛለሁ፣ የማልስማማበትን እሞግታለሁ፡፡ ለበዕውቀቱ የመጻፍ ነጻነት ግን ጥA፡

No comments:

Post a Comment